ከዛሬ ጀምሮ መቻል የሚለውን የቀድሞ ስሙን ማግኘቱ የተረጋገጠው የሊጉ ክለብ በሁለቱም መስመሮች መጫወት የሚችለውን ተከላካይ አስፈርሟል።
ያለፉትን ዓመታት መከላከያ በሚል ስያሜ ሲጠራ የነበረው ክለብ በቀጣዩ የውድድር ዓመት የቀድሞ ስሙን እንደሚያገኝ ከወራት በፊት ዘገባ ሰርተን እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ህጋዊ የሆኑ ጉዳዮች ተጠናቀው ክለቡ በቀጣዩ ዓመት የሚወዳደርበት ስም መቻል ስፖርት ክለብ እንደሆነ በመግለፅ ምዝገባ እያከናወነ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል። በዚህ ስያሜም አዲስ ሎጎ እና የመጫወቻ ትጥቆች እየተዘጋጁ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ በኋላም መገናኛ ብዙሀን መቻል የሚለውን ስም እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ ቡድኑን በአዳዲስ ተጫዋቾች እያዋቀረ የሚገኘው ቡድኑ በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ በሁለቱም መስመሮች እንዲሁም በመሐል ተከላካይ ሚና መጫወት የሚችለውን አህመድ ረሺድ ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ከደደቢት የእድሜ እርከን ቡድኖች የተገኘው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች 2013 ላይ ባህር ዳር ከተማን ተቀላቅሎ ግልጋሎት ሲሰጥ እንደቆየ አይዘነጋም። ዘንድሮም ከፍቅረሚካኤል ዓለሙ በመቀጠል ሁለተኛ አምበል በመሆን ተሹሞ የነበረ ሲሆን ውሉ ከክለቡ ጋር በመጠናቀቁ ከቀድሞ አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝ ጋር አብሮ ለመስራት የአንድ ዓመት ፊርማውን አኑሯል።
የመቻል አዲሱ አርማ