“አንድነታችን እና የቡድን መንፈሳችን ጥሩ ነበር” ሰናይት ቦጋለ
“ዓመቱ ደስ የሚል ነበር” እፀገነት ብዙነህ
የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሦስት የተለያዩ ከተሞች በአስራ ሦስት ክለቦች መካከል ሲደረግ ሰነባብቶ የመጨረሻ ከተማ በሆነችው አዳማ ከተማ በትናንትናው ዕለት ፍፃሜውን ማግኘት ችሏል፡፡ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ጨምሮ በድምሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአምስተኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በክለቡ ውስጥ የሚገኙ ሦስት ተጫዋቾች ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር ዋንጫ በማንሳት የተለየ ታሪክን አስመዝግበዋል፡፡
በደደቢት ፣ በአዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በመጫወት ስድስት ዋንጫዎችን ያገኙት አጥቂዋ ሎዛ አበራ ፣ አማካዩ ሰናይት ቦጋለ እና የመስመር ተከላካዩዋ ዕፀገነት ብዙነህ የታሪኩ ተጋሪ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ቀደም ባለው ቃለ ምልልሳችን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና የታሪኩ ባለቤት መሆን ከቻለችው አጥቂዋ ሎዛ አበራ ጋር ያደረገውን ቆይታ ወደ እናንተ ያደረስን ሲሆን አሁን ደግሞ ከሰናይት ቦጋለ እና እፀገነት ብዙነህ ጋር የነበረን ቆይታ እንዲህ ይነበባል።
ስለ ውድድር ዘመኑ…
ሰናይት “ዓመቱ በጣም ከባድ ነበር ከሌላ ቀኑ ለየት ያለ እጅግ ፈታኝም ነበር ለእኛ፡፡ በመጨረሻም ግን ዋንጫውን በማሳካታችን ደስ ብሎኛል ጥሩ ነበር፡፡”
እፀገነት “ዓመቱ ደስ የሚል ነበር፡፡ ቻሌንጅ የተሞላበት ጨዋታዎችን ነበር ያሳለፍነው ከእግዚአብሔር ጋር ግን አሸናፊዎች ሆነናል፡፡”
ቡድኑ ዳግም የዋንጫ ባለድል ስለሆነበት ሚስጥር…
ሰናይት “ሚስጥሩ አንድነታችን እና የቡድን መንፈሳችን ጥሩ ነበር ፤ ከአምናው ለየት ይል ነበር። ይሄም ነገር ይመስለኛል ቻምፒዮን በተከታታይ እንድንሆን ያደረገን፡፡ ፐርፎርማንሳችንም ከዓመት ወደ ዓመት እየተሻለለ ስለሄደ ውድድሩም ደግሞ እየከበደ ነበር የመጣው። በአጠቃላይ ከባድ ውድድር ነበር ቢከብደንም አሳክተነዋል ፤ ተወጥነዋልም፡፡”
እፀገነት “ቻምፒዮን የሆንበት ትልቁ ምክንያት አንድነታችን እና የቡድን ህብረታችን አሪፍ ስለነበር ነው ፤ ከችሎታ ባሻገር፡፡”
ንግድ ባንክ አምስተኛ ዋንጫን ሲያነሳ ስለተሰማቸው ስሜት…
ሰናይት “ቻምፒዮን መሆን በጣም ከባድ ነው፡፡ ተከታታይ ደግሞ አምስት ጊዜ ክለቡ ቻምፒዮን ሲሆን ደግሞ ከባድ ነገሮችን አሳልፎ ነው የመጣው እና ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ እዚህ ቡድን ውስጥ ሆኜ ቻምፒዮን በመሆኔ ዕድለኛም ነኝ ደስተኛም ነኝ፡፡”
እፀገነት “በድጋሚ ወደ እዚህ ክለብ መጥቼ ቻምፒዮን በመሆኔ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ አንዳንዴ ቻምፒዮንነትን ውስጥህ ከተላመደ ከእዛ ሪትም ውስጥ ላለመውጣት ትጥራለህ። ይሄ ቡድን ደግሞ ድልን ስለለመደ አሁንም በድጋሚ ቻምፒዮን ሆኗል፡፡”
ስድስት ዋንጫን ከሦስት ክለቦች ጋር ስለ ማንሳታቸው…
ሰናይት “እኔ ሁሌም ለየት ያለ ስሜት ነው የሚሰማኝ። የዘንድሮው ደግሞ ይለያል ፤ ለስድስተኛ ጊዜ መብላት ማለት በጣም ከባድ ነው፡፡ ክለቡ ደግሞ ሁሌም አሸናፊ እንድትሆን ነው የሚፈለገው አይደለም ቻምፒዮን በየጨዋታው ማሸነፍን ነው የተለመደው። በቡድኑ ላይ ይሄንንም ነው ማስቀጥል የቻልነው”፡፡
እፀገነት “ስሜቱ እጅግ ደስ ይላል ለስድስተኛ ጊዜ ዋንጫ ስበላ የስኬቴ ምንጭ ክርስቶስ ነው፡፡ ሁሌም በስኬቴ ውስጥ ስላለ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ስሜቱ ዘንድሮ የተለየ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡”