ሻምፒዮኑ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ይናገራል

👉”ተጫዋቾቼ ጀግኖች ናቸው ፤ ትክክለኛ ባለሙያን የሚሰሙ ክለባቸውን የሚያገለግሉ ፣ ለሀገራቸውም ሟች ናቸው።”

👉”ወንዱ ሸራተን ይሸለማል ፤ ሴቱ ላይ ግን ሜዳ ላይ እንኳን 34 ላገባችው ሎዛ አይነገርም።”

👉”እኔ 23 ዓመት የሰራሁ ባለሙያ ነኝ ፤ በማንም ማስፈራራት የምረበሽ ሰው አይደለሁም”

👉”በ11 ዓመታት ውስጥ 5 ዋንጫ ማሳካት የቻለ ጠንካራ ቡድን ነው ያለን”


👉”ሀገራችን ወክለን እንደመወዳደራችን በቅርቡ አትሌቶቻችን እንዳስመዘገቡት ውጤት ሀገራችንን ማኩራት እንፈልጋለን”

የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በዛሬው ዕለት በይፋ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀድሞ የሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በደማቅ ስነ-ስርዓት ዋንጫውን ተረክቧል። ውድድሩን ሽፋን ሰጥታ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ስታደርስ የነበረችው ሶከር ኢትዮጵያም ከሻምፒዮኑ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር ቆይታ አድርጋለች። ብርሃኑ 2004 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከያዘ በኋላ አንድ የጥሎ ማለፍ እና ሁለት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ጨምሮ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከፍ ማድረግ ችሏል። የውድድር ዓመቱ ጉዞን የተመለከተው ቆይታችንም እንደሚከተለው ይቀርባል።

ውድድሩ እንዴት ነበር?

ውድድሩ በጣም ፈታኝ እና አስቸጋሪ ነው። ከዓምናው ዘንድሮው ሁሉም ክለብ ተሻሽሏል። ባለፈው ዓመት ሁሉም ክለብ ከሜዳ ውጪ እኛ እንድንሸነፍ በጋራ ተባብሮ የመጨፈር ባህሪ ነበረው። አሁን ግን ሲታገሉን የነበረው ሜዳ ላይ ነው። ተጫዋቾቹም ፣ አሰልጣኞቹም ተሻሽለዋል። ይህንን ፈታኝ ውድድር ደግሞ አሸንፈን መውጣታችን በጣም ደስ ብሎኛል።

ፈታኞቹ ነገሮች ምን ነበሩ?

የመጀመሪያው ኬንያ ላይ ነበርን ፤ ከስምንት ወር በኋላ ነው ወደ ውድድር የሄድነው። ልጆቼ እንግዲህ ምን ያህል የተደራረበ ኃላፊነትን እንደወሰዱ ሲታይ ለብዙ ባለሙያ አስተማሪ ነው ብዬ አስባለሁ። በማግስቱ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ስለነበረባቸው ለእሱም ከዚህ የተመረጡ ልጆች ነበሩ። ሌላው ደግሞ ለአፍሪካ ዋንጫ እኔ በያዝኩበት ጊዜ ከአስር ልጆች በላይ ነበሩ። ከዛም ደግሞ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ 180 ደቂቃ ሲቀርም የተደራረበ ውድድር ነበር ፤ ሀዋሳ ላይም ውድድሮች ነበሩ። ከሀዋሳ በኋላ ደግሞ ባህር ዳር ነበር። በቅርብ ጊዜ በነበረው ሦስተኛ በወጣንበት የምስራቅ አፍሪካ ውድድርም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልጆች ነበሩ። ሌላው ክለብ በዚህ አጋጣሚ ዕድለኛ ነው ፤ መስራት የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። እኛ ግን መስራት አንችልም። ሰባት ወይ አምስት ልጆች ደግሞ ቤስት ውስጥ ይገባሉ። የጨዋታ መደራረብ እዚህ ብቻ ሳይሆን ሀገራቸውን ለማገልገልም ሲሄዱ የትም ቦታ ሲሆኑ አሰልጣኙ የሰጣቸውን ነገር ይቀበላሉ ብዬ አስባለሁ። ከዛ ከተመለሱ በኋላ የስድስት ቀን ጊዜ ብቻ ነበር። እኔ የሰጠኋቸው የንግድ ባንክ ዓላማ በደንብ እንዲገባቸው ከሽንፈት ፈተና እንደወጡ ነው የምትመለከተው። በየሁለት ቀኑ ነበር ፤ ሌላው ክለብ ዕድለኛ ነው። አንድ ያስመረጠ አለ ፤ ሁለት ያስመረጠ አለ ፤ ያላስመረጠ አለ። ቤቱም ሆነ ሜዳ ላይ በደንብ ተዘጋጅቶ ይመጣል። እኛ ግን አልታደልንም እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ለማድረግ። ባንክ ካለው ዓላማ ራሱንም ማገልገል ስላለበት። ይሄ የተደራረበ ጫና ተቋቁመው አሸንፈን ወጥተናል። ዘራፍም ደግሞ አንልም ፤ በየሜዳው አንፎክርም። አጨብጭቡልንም አንልም። ሲሰድቡንም ዝቅ ብለን አመስግነን ስንሸነፍም ደግሞ እሺ ብለን ነው። ስንሸነፍ እኛ ወደራሳችን ነው የምናየው። ትልቁ ችግር ሌላው እኛን ነው የሚያየው። ይሄ ሁሉ የጫና እና ኃላፊነት ከመውሰድ አንፃር ነው። ይሄን ሁሉ ተደራራቢ ነገር ወስደን አሸናፊ ሆነናል።

በዚህ አጋጣሚ ልጆቼ ጀግኖች ናቸው ፤ ትክክለኛ ባለሙያን የሚሰሙ ክለባቸውን የሚያገለግሉ ፣ ለሀገራቸውም ሟች መሆናቸውን መግለፅ እፈልጋለሁ። ሀለት ሦስት ወር ቤታቸው ተኝተው ሳይሆን ከተደራራቢ ጫና መጥተው ውጤታማ መሆን እንደባለሙያ እኔን ያኮራኛል።

ለውድድሩ የተሰጠውን ትኩረት በተመለከተ ሀሳብህን አጋራን?

እኔ 24 ዓመት አሰልጥኛለሁ። ስድስት ሥራ አስፈፃሚ አይቻለሁ። ለሴቶች የሚያስብ ሥራ አስፈፃሚ መምጣት አለበት ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በፊትም አሉ ፤ አሁንም አሉ ፤ እያነፃፀርኩ ነው። ከአምና ጀምሮ ግን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ቡድን ላይ የሚያደርገውን ወደ ክለብ ትቷል። እኔ እንኳን ከዚህ በፊት ተናግሬያለሁ። ስለሽልማቱ አንስቼ ፌዴሬሽኑን ትሰድባለህ ተብዬ ነበር። የእኔ ከብሔራዊ ቡድን መነሳት ትክክል ነው። የእኔ መነሳት ግን እንዴት እኛ ጋር ሆኖ ስለሽልማት ይጠቃል ብሎ ለጠየቀው አካል ግን ይሄ ውጤት እና የኔ ስራ መልስ ነው። እኔ በጣት አልመጣሀም በጣትም አልሄድም። እዛ ውስጥ በተለይ ፕሬዚዳንቱን በጣም አከብራቸዋለው። ለሴቶች እግርኳስ ያስባሉ ብዬ አስባለሁ። አሁን በቅርብ ጊዜ በሴቶችእግርኳስ ላይ እየተሰራ ባለው ግን ራሳቸውን ቢመረምሩ እላለሁ። እንቀጣሀለን ፣ በደብዳቤ እንጠራሀለን የሚል ዛቻ ደርሶብኛል ፤ እኔ አልፈራም። ምክንያቱም የሴቶች እግርኳስ በኢትዮጵያ እንዲታወቅ ያደረኩት እኔ ነኝ። 23 ዓመት የሰራ ባለሙያ የለም። ወንዶችን ሲያገኙ ሮጠው ሄደዋል ፤ እኔ አልሄድኩኝም። እኔ የጠየኩት አምና ለምን ኮከብ ግብ አግቢ አልተሰጠም ? ነው። 15 ወር ነው ፤ ያሳዝናል። ኮከብ አሰልጣኝ ለምን አልተሰጠም ? ለክለቡ ለምን አልተሰጠም ? ብዬ ነው የጠየኩት። ግን ውድድር እና ሥነስርዓትን እንዴት ትገልፃላችሁ ? ተብሎ እኔ በሚዲያ በመናገሬ ሰበታ ላይ ኮከብ ተጫዋች ኮከብ ጎል አግቢ አንደኛ ዲቪዚዮን አልተናገሩም ፤ እኔ እንዳልናገር። አሁን ይሄ ውድድር ስለእውነት ለመናገር ፕሪምየር ሊግ ይመስላል ? ተራ ፕሮጀክት ነው የሚመስለው። ሊጉ አስር ዓመት ተቋቁሟል። በአስር ዓመት ውስጥ አምና ነው ለኮከቦች ሽልማት ያልተሰጠው። እኔ ይሰጠኝ አይደለም። እኔ ይቅርብኝ ፤ እንኳን እሱን ብሔራዊ ቡድኑንም ሀቅ በመናገሬ እናሳይሀለን ብለው አሳይተውኛል። እኔ ጉዳዬ አይደለም በ 14 ዓመት ውስጥ ስምንቴ ተባርሬያለሁ። አሁንም ብሔራዊ ቡድንንም ክለብንም ማቆም ካለብኝ አቆማለሁ ፤ የሴቶች እግርኳስን የሚነካ ከመጣ። 15 ወር እንዴት ነው የማይሸልሙት ? ይሄ መብት ነው። እስኪ ቆመው ፊት ለፊቴ ይናገሩ። ታሪኬን ነው ያበላሹት ፤ ታራካቸውን ነው ያበላሹት። ወንድ ቡድን እኮ እሁድ ሽልማት ተሰጣቸው ሐሙስ ዕለት ሱፍ ለብሰው አምሮባቸው ታዩ። እነዚህ ልጆች አይደሉ እንዴ ብሔራዊ ቡድን እንዲያገለግሉ የሚሰጣቸው ? ሀገርን የሚያስጠሩት ? ያሳዝናል ! ዘንድሮ ደግሞ በጣም በሚያሳዝን እና በሚገርም ሁኔታ ሽልማቶች አልተሰጡም። እኛ ስንናገር እንዴት ተናገራችሁ ይሉናል። እሺ ኢቢሲ ምንድነው ለእኛ ? እናመሰግናለን ሴቱን ወንዱን ዕኩል ስላደረገ። ኢቢሲ ተባባሪ ነው እንጂ ባለቤት አይደለም። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባለቤትም ናው አባትም ነው። ወንዱ ሸራተን ይሸለማል ሴቱ ግን ሜዳ ላይ እንኳን 34 ያገባቸው ሎዛ አልተነገረላትም። ይሄንን እኔ 23 ዓመት አሰልጥኜ ዝም ብዬ ልየው ? ሽልማት ለምን አልተሰጠም ብሎ ብርሀኑ ደብዳቤ ፅፎ ፌዴሬሽኑን ተናገረ። ብሔራዊ ቡድኑን ዕድሜ ዘላለሜን አይስጡኝ ፤ መነሳቴ ተገቢ ነው። በሴቶች እግርኳስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኢንጅነር ግዛው ጊዜ ነው ሴት ዳኛ የወጣው ፣ ሴት ኳስ ተጫዋቼች የወጡት ፣ ሴት ብሔራዊ ቡድን የተቋቋመው። በሳህሉ ጊዜ እንጀራ እንድንበላ እና ከስደት እንድንመለስ ሆኗል። አቶ ሳህሉ እኔን በግሌ አልጠቀመኝም። እኔ እና ሳህሉ ተካሰናል። ከሴቶች የሰሩትን ነገር ግን ያንን ስራ አስፈፃሚ ማመስገን እፈልጋለው። በአደባባይ ከሶኝ ምልልስ ውስጥ ገብቷል። የእኔን ክብር አደለም የማየው ፤ ግን ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ መጥቶ አልቅሶ ፕሪምየር ሊግ መቋቋም አለበት ብሎ የሲ ብድኖች ፈርሰው የሴቶች እንዲያዙ አድርጓል። በዚህ እናመሰግናቸዋለን። ከዛ በነአቶ ጁነዲን ጊዜ የነበረው ነገር ይታወቃል። አሁን ብሔራዊ ቡድን ላይ ትኩረት አለ። ይሄንን ትኩረት ክለቦች ጋር ማምጣት ያስፈልጋል። ይሄ ውድድር ሐምሌ ላይ ማለቅ ነበረበት? የወንዶቹ መስከረም 20 ይጀመራል ይባላል ፤ እኛ ግን መቼ እንደሚጀመር አናውቅም።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽንን በዘንድሮ የውድድር ዘመን በሁለት መልኩ የተሻሻለ ነበር ብለን መውሰድ እንችላለን ፤ አንደኛው የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ባላቸው አቅም በሙሉ ከእኛ ጋር ነበሩ በተጨማሪም በፌደሬሽኑ ማህበራዊ ትስስር ገፆች በኩል ስናገኝ የነበረው ሽፋን ጥሩ የሚባል ነበር። በሌላው በኩል ግን ድጋፍ አልተደረገልንም።

ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ጭምር ኮከቦችን ይሸልም የነበረው ፌደሬሽኑ ዘንድሮ ግን በሚያሳዝን መልኩ ምን ዓይነት ነገር አልተመለከትንም በሂደት እግር ኳሱን ወደዚህ ዝቅታ መድረሱ ያሳዝናል። ከዚህ ባለፈ ሀሳብ መስጠት እንደወንጀል የሚታይበት ዘመን ላይ ደርሰናል ሀሳብ የሚሰጥን ሰው በቡድን እያሳደዱ ማስፈራራት የትም አያደርሰንም እኔ 23 ዓመት የሰራሁ ባለሙያ ነኝ በማንም ማስፈራራት የምረበሽ ሰው አይደለሁም አሁንም ቢሆን ለእግር ኳሱ መሻሻል መናገሬን እቀጥላለሁ።

የዘንድሮ ቡድን ምን የተለየ ነገር ነበረው?

በ11 ዓመታት ውስጥ 5 ዋንጫ ማሳካት የቻለ ጠንካራ ቡድን ነው ያለን ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው ሂደት ተተኪዎችን በማብቃት ረገድ ትንሽ ክፍተቶች ነበሩብን አሁን ላይ ግን ለተሻለ ስኬት ወጣት ተጫዋቾችን በሚገባ አሰባጥረን ይዘናል። ቡድናችን በመከባበር እና መደማመጥ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ህብረት ባለቤት የሆነ ቡድን ይዘን ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችለናል።ዘንድሮ ላይ ልጆቹ ላይ ያየነው ነገር በቀጣዩቹም ዓመታት የተሻለ ውጤት እንደምናመጣ ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል። እንደ ንግድ ባንክ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውጤታማ የመሆናችን ሚስጥር ከሌሎች ክለቦች ፍፁም በተለየ መልኩ ሁሉም የክለቡ አካላት የራሱን ድርሻ ጠንቅቀን የመስራታችን እና ሁሉም በሌላው ስራ ላይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ያለመኖሩ ነገር ስኬታማ አድርጎናል።

በቀጣይ ለሚጠብቃችው አህጉራዊ ውድድር በምን አይነት መንገድ እየተዘጋጃችሁ ነው?

ዋንጫውን ካረጋገጥንበት ቀን አንስቶ አልተኛንም ከስድስት አዳዲስ ተጫዋቾች ጋር ቅድመ ስምምነት ፈፅመናል ከቀናት በኃላ ይቀላቀሉናል የመለመልናቸው ልጆች U-20 ተጫዋቾች የነበሩ ይገኙበታል ታድያ እነዚህ ተጫዋቾች ካሉን ጋር ሲጣመሩ የተሻለ ያስጉዙናል ብለን እንጠብቃለን። ዓምና ጥሩ ውጤት ነበረበን ምንም እንኳን ዓምና የተሻለ የመዘጋጃ ጊዜ የነበረን መሆኑ ሳይዘነጋ ዘንድሮ ግን ከውድድር ነው በቀጥታ የምንሄደው ሌላው መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ውድድር በራሱ በጣም አድካሚ ነው ከአየር ንብረቱ ሞቃታማነት ጋር ተዳምሮ በሁለት ቀናት ልዮነት ጨዋታ ማድረግ በራሱ በጣም ፈታኝ ነው።ሀገራችን ወክለን እንደመወዳደራችን በቅርቡ አትሌቶቻችን እንዳስመዘገቡት ውጤት ሀገራችንን ማኩራት እንፈልጋለን ፤ ዘንድሮ ደግሞ ምስራቅ አፍሪካን ወክለን ወደ ሞሮኮ ማምራት እንፈልጋለን ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየተዘጋጀን ነው ላለፉት ሁለት ቀናት ለልጆች እረፍት ሰጥተን ነበር ነገርግን ከነገ ረፋድ አንስቶ ወደ ዝግጅት ዳግም የምንገባ ይሆናል።