ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አነሳ

በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነበትን ዋንጫ አንስቷል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳሰ ፌድሬሽን ስር የሚደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን በአስራ ሦስት ክለቦች መካከል በየጊዜው ሲቆራረጥ ሰንብቶ በመጨረሻም በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ጅምሩን ካደረገ በኋላ በባህርዳር እንዲሁም የሁለተኛው ዙር ሙሉ ጨዋታዎች በአዳማ ከተማ በሁለት ስታዲየሞች ሲከናወን ከርሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለአምስተኛ ጊዜ ቻምፒዮን አድርጎ ተደምድሟል፡፡ ውድድሩ ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው የመዝጊያ ሥነ ስርአት ላይ የመጨረሻ ጨዋታ ሁለተኛ ሆኖ ዓመቱን የፈፀመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታቸውን አከናውነው በኤሌክትሪክ አሸናፊነት 3ለ1 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተለያዩ ሽልማቶች የተደረጉ ሲሆን በክብር እንግድነትም ወ/ሮ ነሲሳ አልመሀዲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፈሪሀ መሀመድ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር አማካሪ ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ አቶ አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ፕሬዝዳንት የስፖርት ክለብ የበላይ ጠባቂ ፣ የሴቶች ልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ እና አቶ ባህሩ ጥላሁን የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተለያዩ የሽልማት መርሃግብሮች ተካሂደዋል፡፡

አስቀድሞ ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ፣ ተቋማት እና ድርጅቶች የሽልማት መርሀግብር የተከናወነ ሲሆን በመቀጠልም ለዕለቱ ዳኞች የሜዳሊያ ስጦታ ከተበረከተ በኋላ ውድድሩን በ63 ነጥቦች አንደኛ ሆኖ የፈፀመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወርቅ ሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ሶስተኛ ሆኖ በመፈፀም የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፊት መስመር አጥቂዋ ሎዛ አበራ በ34 ጎሎች የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ስታጠናቅቅ የቦሌ ክፍለከተማ ቡድን ዓመቱን የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ በመሆን መርሀግብሩ ተደምድሟል፡፡