ዋልያዎቹ በቻን ማጣሪያ ወደ መጨረሻ ዙር አልፈዋል

ታንዛንያ ላይ ከደቡብ ሱዳን ጋር ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት ዋልያዎቹ 5-0 በመርታት ወደ ሩዋንዳው የመጨረሻ ማጣሪያ ጨዋታ አምርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለ ግብ ከተጠናቀቀው የመጀመሪያ ጨዋታ አጥቂ ስፍራ ላይ ቸርነት ጉግሳን በብሩክ በየነ ቦታ በመተካት ዳዋ ሆቴሳን የፊት አጥቂ አድርጎ ጨዋታውን ጀምሯል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ቀርቦ መጫወት ችሏል። ቡድኑ የ17ኛው ደቂቃ ላይ ባደረገው አደገኛ ሙከራ አስራት ቱንጆ በቀኝ አጥብቦ ገብቶ ያሳለፈለትን ቸርነት ጉግሳ ከቅርብ ርቀት ሞክሮ ወደ ላይ ተነስቶበታል። 26ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት የገጠመው ሱራፌል ዳኛቸውን በከነዓን ማርክነህ የተካው ብሔራዊ ቡድኑ የደቡብ ሱዳንን የመልሶ ማጥቃት ከመነሻው እያቋረጠ የኳስ ቁጥጥር ጫናውን ከፍ አድርጎ መጫወቱን ቀጥሎ የከታታይ ግቦችን አስቆጥሯል።

ዋልያዎቹ 33ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የጀመሩትን ጥቃት ወደ ግራ ባዞሩበት ቅፅበት ከአማኑኤል ዮሐንስ የተነሳውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ሲጨርፍለት ረመዳን የሱፍ ራሱን ነፃ አድርጎ በመሮጥ ጎል አድርጎታል። በዛው በግራ መስመር ከአንድ ደቂቃ በኋላ ረመዳን የሱፍ ወደ ሳጥን ያደረሰውን ኳስ ከነዓን ማርክነህ ከተከላካይ ጋር ታግሎ ሲያስቀርለት አማኑኤል ገብረሚካኤል ማስቆጠር ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ደቡብ ሱዳኖች ከቆሙ እና ከቀጥተኛ ኳሶች የተሻለ ጫና ፈጥረው ታይተዋል።

 በቁጥር በርክተው ግብ አፋፍ የደረሱባቸው አጋጣሚዎችም ተፈጥረው የነበረ ሲሆን ዋልያዎቹ ተረባርበው አውጥተዋቸዋል። ዋልያዎቹ ቀስ በቀስ ወደ ቀደመ ቁጥጥራቸው ሲመለሱ 55ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ድኖበታል።

ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ቀኝ መስመር ያደላ ጥቃቱ ተደጋግሞ መታየት ሲጀምር 66ኛው ደቂቃ ላይ ከዚሁ አቅጣጫ አማኑኤል ገብረሚካኤል ያስጀመረው ጥቃት በደቡብ ሱዳኖች ቢቋረጥም አማኑኤል ዮሐንስ በድጋሚ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አስቀጥሎት ዳዋ ሆቴሳ በመቀበል ከግራ ወደ ውስጥ ሲመልሰው የደቡብ ሱዳኑ ተከላካይ ፒተር ሜከር በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል።

በቀሪ ደቂቃዎች አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አራት ቅያሪዎችን ሲያደርጉ ከእነዚህ መካከል የሆነው በረከት ደስታ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከዳዋ የደረሰውን ኳስ ነፃ ሆኖ ሞክሮ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። ሆኖም ከአንድ ደቂቃ በኋላ በረከት በቀኝ መስመር ከይገዙ ቦጋለ ጋር አስደናቂ አንድ ሁለት ተጫውቶ ይገዙ ያሳለፈውን ሌላኛው ተቀያሪ መስዑድ መሐመድ ጎል አድርጎታል። በጭማሪ ደቂቃ በግራ መስመር በከፈቱት ሌላ ፈጣን ጥቃት መስዑድ መሐመድ ያሳለፈውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ የማሳረጊያ ጎል አድርጎታል።

ጨዋታው 5-0 መጠናቀቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ከሩዋንዳ ጋር ለሚጠብቀው የመጨረሻ የቻን ማጣሪያ ጨዋታ ማለፍ ችሏል።