በሴካፋ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ተካፋይ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድሩ ላይ ጠንካራ ሆኖ ለመገኘት ይረዳው ዘንድ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ አካቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን ከቀናት በፊት ለአምስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ክለቡ የሊጉን ዋንጫ ከፍ በማድረጉ በቀጣዩ ወር ነሀሴ 7 በታንዛኒያ (አሩሻ) በሚደረገው የሴካፋ የክለቦች የቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ሀገራችንን በመወከል ይሳተፋል፡፡ በውድድሩ ላይ ክለቡ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት በአዳማ ከተማ ማረፊያውን በጄ ሪዞርት በማድረግ ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን አዳዲስ ስድስት ተጫዋቾችንም ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡
በሀዋሳ ከተማ በመጫወት ያለፉትን አራት ዓመታት ቆይታ የነበራት የመሀል ተከላካዩዋ ቅድስት ዘለቀ ፣ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከተገኘች በኋላ በአዳማ ከተማ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያሳለፈችው የመስመር ተከላካዩዋ ናርዶስ ጌትነት ፣ ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ሦስት ዓመታትን በድሬዳዋ ከተማ በመጫወት ቆይታ የነበራት የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቿ ብርቄ አማረ ፣ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከተገኘች በኋላ በ2013 በንግድ ባንክ ዘንድሮ ደግሞ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በአማካይ ስፍራ ስትጫወት የተመለከትናት ንቦኝ የን ፣ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ስልጠናዋን አጠናቃ ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የተመለከትናት አጥቂዋ አሪያት ኦዶንግ እና በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ፍሬ የሆነችው እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጠናቀቀውን የውድድር ጊዜ ደግሞ በመከላከያ ቆይታ የነበራት የግራ መስመር አጥቂዋ መሳይ ተመስገን አዲሶቹ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ንግድ ባንክ ፈራሚዎች ናቸው፡፡
ቡድኑ በቀጣዮቹ ቀናት በክለቡ ከሚገኙት ህይወት ደንጊሶ ፣ ጥሩአንቺ መንገሻ ፣ ፎዚያ መሀመድ እና አለምነሽ ገረመው እንዲሁም ተጨማሪ ሌሎች ተጫዋቾችም ጋር እንደሚለያይም ይጠበቃል፡፡