ዛምቢያ 2017፡ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አባላት ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ ስለሚፈጥረው ስሜት ይናገራሉ 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ አንደኛ ዙር እሁድ ሶማልያን ያስተናግዳል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት 26 ተጫዋቾችን በመያዝ ለእሁዱ ጨዋታ እየተዘጋጀ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ድንቅ አቋም በማሳየት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ተካተዋል፡፡

ሃላባ ከተማን ለቆ ወላታ ድቻን የተቀላቀለው ፈቱዲን ጀማል ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ መልካም የውድድር ዘመን ተጠቃሽ ተጫዋቾች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የተከላካይ አማካዩ ዘሪሁን ብርሃኑ እና ባለክህሎቱ የጅማ አባ ቡና የመስመር አማካይ ዳዊት ተፈራ ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ ስለሚፈጥረው ስሜት እና ስለ እሁዱ ጨዋታ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

ፈቱዲን ጀማል

“በብሄራዊ ቡድን በመመረጤ ደስተኛ ነኝ፡፡  ማንም ሰው ለሃገሩ መጫወት ይፈልጋል፡፡ ያለኝ ስሜት ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ነገር እንደምሰራ አምናለሁ፡፡ በብሄራዊ መጠራቴ ወደ ፊት ለሚኖረኝ የእግርኳስ ህይወት ጥሩ እንድሰራ መነሳሳት ይፈጥርብኛል፡፡ ለወታት ቡኑ መጫወቴ አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ ለዋናውም ብሄራዊ ቡድን እንድዘጋጅም ያደርገኛል፡፡

“ለእሁዱ ጨዋታ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ማንኛውም ተጋጣሚ ወደ ሜዳ ሲገባ 11 ለ 11 ሆኖ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሶማልያን በቀላሉ እንደምናሽንፍ ሊያስብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሶማልያን የምናቀልበት ለሌሎች ከፍ ያለ ግምት የምንሰጥበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እሁድ በጥሩ ሁኔታ ተጫውተን እንደምናሸንፍ ነው የምናስበው፡፡”

ዘሪሁን ብርሃኑ 

“ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ የሚያኮራ ነገር ነው፡፡ የየትኛውም ተጫዋች የመጀመርያ አላማ ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ ነው፡፡ በመመረጤ ደስተኛ ነኝ፡፡ በቀጣይም ተግቼ እንድሰራ ያደርጋል፡፡ ለወጣት ቡድኑ መመረጤ ወደፊት ለብሄራዊ ቡድን እንድንታይ ከሌሎች አንጻር እድል ይፈጥራል፡፡ ለወደፊት እግርኳስ ህይወቴም መሰረት ነው፡፡

“ዝግጅት እደረግን ያለነው ለሶማልያው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ዋንጫው ለመሳተፍ ነው፡፡ ነገር ግን ለሶማልያ ጥሩ ግምት እሰንሰጣለን ምክንያም እግርኳስ ነው፡፡ በእግርኳስ የሚፈጠረው ነገር አይታወቅም፡፡”

ዳዊት ተፈራ

” ለብሄራዊ ቡድን የሚፈጥረው ስሜ ደስ የሚል ነው፡፡ ከመጫወት ባለፈ መጠራቴ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለወደፊት የእግርኳስ ህይወቴም ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

“ለእሁዱ ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት እደረግን እንገኛለን፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም እየተሸሻልን ነው፡፡ እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *