ከሰሞኑ በኢምሬትስ የተሳካ ህክምናን በማድረግ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ኢንስተራክተር አብረሃም መብራቱ በካፍ ጥሪ መሠረት ፈተናን ለመስጠት ወደ ማላቦ ዛሬ ያመራሉ፡፡
ኢትዮጵያዊው ኤሊት ኢንስትራክተር አብረሃም መብራቱ ቀጣዩን የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመንን ከባህርዳር ከተማ ጋር እንደሚቀጥሉ ይታወቃል፡፡ ኢንስትራክተሩ ከሰሞኑ ለአንድ ሳምንት ያህል በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በጉልበታቸው ላይ የደረሰባቸውን ህመም በተሳካ ሁኔታ ታክመው ወደ ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ በካፍ ጥሪ መሠረት ወደ ማላዊ ያመራሉ፡፡
በካፍ ስር ከሚገኙ ኤሊት ኢንስትራክተሮች መሀል አንዱ የሆኑት ኢንስትራክተሩ በማላዊ እየተሰጠ የሚገኘውን የካፍ ቢ ላይሰንስ የአሰልጣኞች የስልጠና ኮርስን ካፍ እንዲገመግሙ እና አጠቃላይ ፈተናን እንዲሰጡ ጥሪ ስላስተላለፈላቸው ለአምስት ቀናት ያህል በቦታው ለመቆየት በዛሬው ዕለት አመሻሹን ወደ ስፍራው እንደሚያመሩ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡