ሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ለሴካፋ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ጥሪ ቀረበላቸው

በታንዛኒያ ለሚደረገው የሴካፋ የሴት ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሁለት ኢትዮጰያዊያን ሴት ዳኞች ተጠርተዋል፡፡

ካፍ በአዲስ መልክ ባሳለፍነው ዓመት ከጀመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የሴት ክለቦች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ይደረጋል፡፡ አህጉራዊው ዋናው ውድድር ከመከናወኑ በፊት በየዞኑ የሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከቀጣዩ ወር ጀምሮ መደረግ የሚጀምሩ ሲሆን የሀገራችንን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ በድምሩ ስምንት ሀገራትን የሚያሳትፈው የሴካፋ ዞን የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ከነሀሴ 7 ጀምሮ በታንዛኒያ (አሩሻ) ከተማ መካሄድ የሚጀምር ሲሆን ከንግድ ባንክ ባሻገር ሁለት ሴት ዓለም አቀፍ ዳኞች በካፍ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በዋና ዳኝነት ፀሀይነሽ አበበ በረዳት ዳኝነት ደግሞ ወይንሸት አበራ በዳኝነት መጠራታቸው ታውቋል።