የጣና ሞገዶቹ የሁለት ተጫዋቻቸውን ውል አድሰዋል

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ የሁለት ተጫዋቾቹን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመት አራዝሟል።

በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ካስፈረሙ በኋላ የነባሮቹን ውል ማደስ የያዙት ባህር ዳር ከተማዎች ከቀናት በፊት የአምበላቸው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና የወጣቱን ተጫዋች ጌታቸው አንሙት ውል ያደሱ ሲሆን ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ የተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ቆይታ ለተጨማሪ ዓመት ማራዘማቸውን ይፋ አድርገዋል።

ውሉን ያራዘመው የመጀመሪያው ተጫዋች ሳለአምላክ ተገኘ ነው። በኢትዮጵያ ቡና የክለብ ህይወቱን የጀመረው ሳለአምላክ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ከቀናት በፊት ወልቂጤ ከተማን ለመቀላቀል ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም አመሻሽ ላይ ወደ ባህር ዳር በማቅናት በክለቡ ለመቆየት የሁለት ዓመት ውል አስሯል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ በረከት ጥጋቡ ነው። የቀድሞ የኢኮስኮ፣ አማራ ፖሊስ እና ወልቂጤ ከተማ ተጫዋች ያለፉትን ሁለት ዓመታት በክለቡ ቆይታ ያደረገ ሲሆን አሁንም በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታይ በውሃ ሰማያዊው መለያ ለመዝለቅ ፊርማውን አኑሯል።