ዑመድ ዑኩሪ የኦማኑን ክለብ ተቀላቅሏል

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ዑመድ ዑኩሪ የኦማኑን ክለብ አል-ሱዋይክ መቀላቀሉን ክለቡ ይፋ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጫወት ከሀገራችን የስፖርት ማህበረሰብ ጋር መተዋወቅ የቻለው ባለ ግራ እግሩ አጥቂ 2006 ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እና ኮከብ ተጫዋች በመሆን ከፈፀመ በኋላ ወደ ግብፅ ሊግ በማምራት ለአል-ኢትሀድ አሌክሳንድሪያ ፣ ኤንፒ ፣ ኤል ኢታንግ አል አርቢ ፣ ሶሞሀ እና አስዋን ክለቦች ስድስት ዓመት ከግማሽ ያህሉን በማሳለፍ በ2013 አጋማሽ ወደ ሀገሩ በመመለስ በሀድያ ሆሳዕና መለያ ላለፉት አንድ ዓመት ከግማሽ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጫወት ቆይታን አድርጓል፡፡

ተጫዋቹ ከሀድያ ሆሰዕና ጋር ከሳምንታት በፊት ለመቀጠል ድርድር ማድረግ ቢችልም ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ወደ ግብፅ አምርቶ ለቀድሞው ክለቡ ሶሞሀ ለመጫወት ስለመቃረቡ ሲገለፅ ቢቆይም ወደ ኤዥያዋ ሀገር ኦማን አምርቶ በተጠናቀቀው ዓመት የሀገሪቱን ሊግ በ31 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀውን አል-ሱዋይክ ክለብ በአንድ ዓመት ውል መቀላቀል ችሏል፡፡

አል-ሱዋይክ የኦማን ሊግን አራት ጊዜ እንዲሁም በቀድሞው የሀገሪቱ መሪ የተሰየመውን የሱልጣን ዋንጫን ሁለት ጊዜ የሀገሪቱን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አንድ ጊዜ ማንሳቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡