ፋሲል ከነማ የአማካዩን ውል አድሷል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ የሀብታሙ ተከስተን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመት አድሷል።

በቀጣዩ የውድድር ዓመት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚወክለው ፋሲል ከነማ የነባሮቹን ውል እያደሰ ጎን ለጎን አዳዲስ ተጫዋቾችንም እያስፈረመ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ አማካዩ ሀብታሙ ተከስተ በክለቡ ቀጣዮቹን 24 ወራት ለመቀጠል ፊርማውን አኑሯል።

ከዳሽን ቢራ ወጣት ቡድን የተገኘው ሀብታሙ ወደ ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን እንዲሁም መቐለ ተጉዞ የእግር ኳስ ህይወቱን የቀጠለ ሲሆን ከ2011 ጀምሮ ደግሞ በዐፄዎቹ ቤት ጥሩ ግልጋሎት ሲሰጥ ቆይቷል። ተጫዋቹን ለማስፈረም በርካታ ክለቦች ፍላጎት ቢያሳዩም ያለፉትን አራት ዓመታት በቆየበት መለያ ለመዝለቅ ውል አስሯል።

ያጋሩ