በእንግሊዝ ሀገር ከእግርኳሷዊ ትምህርቶች እና ከሥልጠና ጋር እያሳለፈ የሚገኘው አሰልጣኝ ሚካኤል ኃይሉ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታ ልምዱን ያካፈለባቸውን ኃሳቦች አንስቷል።
ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ በእግርኳሱ ከሜዳ ውጪ ያሉ ጉዳዮች ትኩረት የሚስቡበት ጊዜ ነው። ለከርሞው ቡድናቸውን ለማዋቀር ክለቦች አዳዲስ ተጫዋቾችን የሚያመጡበት እና አሰልጣኞችን የሚሾሙበት እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም በሥራ ላይ ያሉ አሰልጣኞች በምልመላው እና በቀጣይ ቡድን ግንባታ ላይ ትኩረታቸውን ማድረጋቸው የማይቀር ነው። በሌላ በኩል ግን ለነባር አሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ትምህርቶችን ለመውሰድ ፣ የያዙትን የአሰልጣኝነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንዲሁም ወደ ሙያው እንደ አዲስ መግባት ለሚፈልጉ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን ለመውሰድ ክረምቱ ዕድል ይሰጣል።
በከፍተኛ ደረጃ አሰልጣኝነት ላይ ለመድረስ መንገዱ ረጅም እንደሆነ ቢታወቅም ራስን ለማብቃት የሌሎችን ተሞክሮ መውሰድ አጋዥ ነው። የዛሬው እንግዳችንም ከሀገር ውጪ ይኑር እንጂ ለሙያው ባለው ፍቅር እና ፍላጎት መነሻነት ራሱን በትምህርት ሲያሳድግ የቆየ ነው። አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ በአውሮፓ ትምህርቱን ሲከታተል መቆየቱ ደግሞ እሱ ያለፈበት መንገድ አንድም የሀገራችንን የአሰልጣኞች ስልጠና አሰጣጥ ከውጪው አካሄድ ጋር ለማስተያየት ሁለትም በሙያው ህልም ያላቸው ወጣቶች ጥሩ ልምድ እንዲያገኙበት የሚያግዝ በመሆኑ ለንባብ አብቅተነዋል።
እንግዳችን ሚካኤል ኃይሉ ይባላል። በሚሊኒየሙ መግቢያ ላይ በሀዋሳ ከተማ ተስፋ ቡድን እና በሻሸመኔ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በወቅቱ በአሰልጣኝ ስዩም አባተ አማካይነት ለኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን የመጠራት ዕድል ገጥሞት ነበር። እምብዛም ሳይቆይ ወደ ሀገር እንግሊዝ የመጓዝ ዕድል የገጠመው ሚካኤል እዛም በ’Semi Professional’ ቡድኖች ውስጥ መጫወት ችሏል። “ስልጠናቸው ምክንያታዊ ነው ፤ ለምን እንደምትሰራ ታውቃለህ” የሚለው ሚካኤል ወደ አሰልጣኝነት በመሳቡ ቋንቋ ከተማረ በኋላ ራሱን በአሰልጣኝነት ለማብቃት ጎን ለጎን ትምህርት ጀምሯል። በ’personal tranier’ ዲፕሎማን ይዞ በመቀጠል በ’University of South Wales’ ድግሪውን በ’Football Coaching Development and Adminatration’ ሲሰራ በስልጠና ደረጃው ‘B License’ ላይ ደርሷል። በመቀጠል በ ‘Universty of the west of England’ በ’Sport Psychology’ የማስተርስ ድግሪውን ሰርቶ አጠናቋል።
“እኔ የእግርኳስ አሰልጣኝ ነኝ። ሳይኮሎጂ የተማርኩት ከእግርኳስ ሥልጠና ጋር እንደሚገናኝ ስለማምን ነው። ጥሩ በራስ መተማመን እንዲኖረኝ አድርጓል። የቡድን ውህደት እንዴት መፍጠር እንደምችል አውቃለሁ። የራሴን ፍልስፍና እንዳዳብርም ረድቶኛል።” የሚለው ሚካኤል በተከታታይ ትምህርቶች ራሱን ወደ አሰልጣኝነት ሲያመጣ ተጫውቶ ያሳለፈበትን ብሪድፖርት ታውን ከ12 ዓመት በታች ቡድን አሰልጥኖ ያለፈ ሲሆን አሁን ደግሞ የብሪስቶል ሲቲን ከ15 ዓመት በታች ቡድንን እያሰለጠነ ይገኛል።
“እንግሊዝ ውስጥ በዓመት ለጥቂት ሰው ነው የ ‘ኤ’ ላይሰንስ የሚሰጡት ያንን ዕድል ለማግኘት በፕሮፌሽናል ክለብ ውስጥ መስራት ይጠበቅብኛል። በእርግጥ ኢትዮጵያ ሄጄ እንድሰራ ተነግሮኛል። ትምህርት ቤት እያለንም ወጥተን መስራት እንዳለብን ይነግሩን ነበር። ከሀገሬው ሰው በተሻለ ይህ ዕድል እንዳለንም ጭምር ይነግሩን ነበር። ‘ኤ’ እና ‘ፕሮ’ ላይሰንሳችንን ለመስራት ይህ የተሻለው መንገድ ነው። እኔም ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቼ የመስራት ፍላጎት አለኝ። ከእኔ ጋር የሚሄድ ዓይነት ክለብ ባገኝ ደስተኛ ነኝ። በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ማየት እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ።” የሚለው ሚካኤል ሀገር ውስጥ ካሉ የተወሰኑ አሰልጣኞች ጋር ግንኙነት መፍጠሩን እና በቀጣይ ምንአልባትም በመጪው የውድድር ዓመት ወደ ሀገሩ ተመልሶ በማሰልጠን ትምህርቱንም በመቀጠል እስከ ዩኤፋ ፕሮ ላይሰንስ ድረስ መሄድ ዓላማው መሆኑን ይናገራል ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ቀናት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ይጠበቃል።
መቼም አንድ በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ያለ ወጣት ከሀገር ሲወጣ ሰርቶ እንዲለወጥ አልያም በሌሎች ትምህርቶች ላይ ተሰማርቶ በቶሎ ወደ ሥራ እንዲገባ ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሰልጣኝ የመሆን ህልምን ይዞ ቦታ ማግኘት እንደሚከብደው ሁሉ ሰው ሀገር ላይ ሄዶ ከተለምዶው ወጣ ወዳለ የትምህርት ዘርፍ መግባት ቀላል እንዳልሆነ ማሰብ አይከብድም። “ራሴን እዚህ ሀገር ከፍ ባለው ደረጃ ላይ ማግኘት ነው የምፈልገው። ትምህርት ላይ ሳለው አሉታዊ አስተያየቶች ይሰጡኝ ነበር። ‘ለምን ሥራ አትሰራም ?’ የሚሉ ግፊቶች ነበሩ። ዩኒቨርስቲ ውስጥ አምስት ዓመት ሳሳልፍ ያጣዃቸው ነገሮች አሉ። አምላክ ይመስገን እስካሁን የማስበውን አሳክቻለሁ። እዚህ ሀገር ላይ ግን በትልቅ ደረጃ እታያለሁ ብዬ አስባለሁ።” የሚለው የወጣቱ አሰልጣኝ ሀሳብም ይህንን ያስረዳል።
ሚካኤል ለጥቂት ጊዜ ቢሆንም በተጫዋችነት ባሳለፈበት ወቅት የታዘበውን የሀገራችንን የሥልጠና ሁኔታ በሀገረ እንግሊዝ በትምህርት ካሳለፈባቸው ጊዜያት ጋር በማስተያየት ይህንን ብሎናል።
“እዚህ ሀገር እግርኳስ በትህምርት ደረጃ ስትማረው ከብዙ አንግል ነው። ለምሳሌ እኛ ሀገር በመደበኛ ትምህርት የምንማረው ራሱ ዝርዝሮች ውስጥ ከመግባት አንፃር ጥቂት ነው። እዚህ የተለየ መንገድ ነው የሚከተሉት። በምስል ፣ በድምፅ በሌሎችም የሰው ልጅ በሚቀበልባቸው መንገዶች እንድትማር ይደረጋል። ሁለተኛ ብዙ እንድታነብ ትጠየቃለህ። ብዙ አንብበህ ብዙ ዕውቀት ራስህ ይዘህ እንድትመጣ ያረጉሀል። ለምሳሌ ዩኒቨርስቲ በምማርበት ሰዓት ጠዋት በክፍል ውስጥ ተምሬ ከሰዓት ደግሞ በኮሌጆች እና አካዳሚዎች አሰለጥናለሁ። የምንሰራው የሥልጠና ፕሮግራም ሁል ጊዜ ይቀረፃል። ከዛ እያንዳንዱ ነገር ላይ ራስህ ግብረ መልስ ትሰጣለህ። በዛ ላይ ተመስርተው አስተማሪዎችህ ገምግመው የራሳቸውን መልስ ይሰጣሉ። ራስህም ቪዲዮውን አይተህ ምን ጥሩ እንደሰራህ ምን መስተካከል እንዳለበት ታያለህ። እግርኳስን ከብዙ አቅጣጫ ነው የሚያዩት። እኛ ሀገር እንደ አርት ብቻ የምናይበት መንገድ ይበዛል። እዚህ ግን እግርኳስ ሳይንስም አርትም ነው። ያ ትምህርቱን በራሱ ወደኸው እንድትማረው ያደርጋል። አንዳንዴ ጭራሹኑም ኳስ ተጫውቶ የማያውቅ ሰው መጥቶ ይማራል። ምክንያቱም በትምህርቱ ውስጥ ብዙ ዝርዝር ነገሮች አሉ። ነገሮችን መርምረህ እንድታብራራ የሚያደርግ ከዛም አልፎ ስህተቶችህን ራስህ መርምረህ እንድታገኝ ያደርጋል። ለምሳሌ ከእኛ ሀገር አንዳንድ ልጆች ይጠይቁኛል ፤ ለምሳሌ ስለ ታክቲክ ፣ ስለ አሰልጣኝ ፍልስፍና ስለ ፕሪንስፕል ኦፍ ፕሌይ ፤ በእርግጥ እነዚህን ነገሮች በማንበብ ባውቃቸውም ትምህርት ቤት ውስጥ ግን ይሰጣሉ። ለምሳሌ እዚህ ሀገር እግርኳስ ትልቅ ቢዝነስ ነው። ትምህርቱ ውስጥ ይህንን የተመለከተ ኮርስ አለ። በዚህ መልኩ ትምህርቱ እግርኳስን ከአሰልጣኝነት ብቻ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ በጥልቀት እንድትመለከተው የሚረዳ ነው። ያ መሆኑ እንድትማረውም እንድታውቀውም ፍላጎት ያሳድርብሀል።”
ቀጣዩ የወጣቱ አሰልጣኝ ማብራሪያ ከወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በወሰደውን ልምድ ላይ በመንተራስ በአውሮፓ የአሰልጣኝነት ትምህርትን ዕድልን ማግኘት ስለሚፈጥረው ልዩነት ይነግረናል።
“አውቃለሁ እዚህ ሀገር ለመግባት በጣም ይከብዳል። ብዙ ሰዎች ‘እንዴት ነው ኮርስ የምንወስደው?’ ብለው ይጠይቁኛል። በእርግጥ መንገዱ ረጅም ነው። የእኛ ሀገር ሰው ዕውቀት አንሶት ሳይሆን እዚህ ሀገር ዕድሉ ኖሯቸው የገቡ ሰዎች ካሉ ቢማሩ እላለሁ። ከሀገር ቤት ሆነው ተፃፅፈው የሚያገኙበት መንገድ ካለም እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም እዚህ እግርኳስ በተለይ በትምህርት ቤት ደረጃ የተለየ ነገር ነው። ለምሳሌ አምና ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ነበር። ከአንድ ቡድን ጋር ሦስት አራት ቀን ሰርቼ ነበር። ያየኋቸው ጥቃቅን ሳይሆን ትላልቅ ስህተቶች ነበሩ ፤ ተጫዋቾች ላይ በተለይም ባላንስን በተመለከተ። አንድም ተጫዋቾች የሚጎዱት እና በቶሎ የማያገግሙት ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው። እዛ ያሰራኋቸውን እዚህ በተግባር ስለምደጋግመው እኔ እንድለምደው አርጎኛል። በአጠቃላይ እዚህ ስትመጣ እግርኳስ ሌላ ነው። የእኛ ሀገር ተጫዋቾች ኳስ መጫወት ይችላሉ። ግን ኳስ መቻል ብቻ አይደለም እንድትጫወት የሚያደርግህ። ቴክኒኩን ማወቅ ብቻ አይደለም ፤ ሌሎች በጣም ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች አሉ። ለዛ ደግሞ አሰልጣኞች ኃላፊነት አለባቸው። የተጫዋቾችን በራስ መተማመን እና ብቃት የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው። አብዛኛውን ጊዜ ተጫዋች 65-70 በመቶ ራሱን ማሻሻል ቢጠበቅበትም አሰልጣኞች የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ነው። ሌላው ቢቀር የተሻለ የሥልጠና ከባቢ መፍጠር ሲችሉ ተጫዋቾች ለሚሰሩት ነገር እንዲጓጉ ይሆናሉ። ያም የአሰልጣኝነት አካል ነው። እኛ ሀገር አሰልጣኞች ይቆጣሉ ፤ እኔም አውቃለሁ በምጫወትበት ሰዓት ላይ። ያ ነገር እንድትሰራላቸውም አያደርግም።
ያለህን አቅም እንድታወጣ አያደርግም። በእርግጥ ከባህሪ አንፃርም ሊሆን ይችላል። ከትምህርቱ አንፃር ግን በዚህ ረገድ ሊያውቁት የሚችሉት ነገር ይኖራል።”
እርሱ በተማረበት እና በታዳጊዎች ላይ እየሰራ በሚገኝበት እንግሊዝ ሀገር ውስጥ የአሰልጣኝነት መንገዱ ምን እንደሚመስል ሲያስረዳ ደግሞ ይህንን ይላል።
“የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ጥቂት ነገሮችን ነው የሚሰጡህ። ሌላው ቢቀር ከመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ በፊት ሌሎች ኮርሶች ለምሳሌ እንደ ሊደርሺፕ እና ፈርስት ኤይድ ዓይነት ኮርሶችን መውሰድ ይጠይቃል። ከሁለተኛ ደረጃ በኋላ ደግሞ የተወሰነ አሰልጥነህ መመለስ ይኖርብሀል። ያሰለጠንክበትን ማስረጃ ይጠይቃሉ። ‘ሲ’ም ‘ቢ’ም ላይሰንስ ለማግኘት እንዲሁ እየሰሩ መመለስ ይጠይቃል። ምንም ዋሽተህ የምታገኘው ነገር የለም። ምክንያቱም ማንም እንዲሁ ማስረጃ አይፅፍልህም። በዩኒቨሪሲቲ ደረጃ ስትማረው ትንሽ ረጅም ሊሆን ይችላል። የክለብ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የነበሩ ግን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ግን በኮርስ ነው የሚወስዱት። እኔ ትልቅ ክለብ አልተጫወትኩም ተዋቂም አልነበርኩም። ስለዚህ ኖርማል ሰው ስትሆን እና በዩኒቨሪስቲ ደረጃ ስትወስደው የኳሱ እውቀት ይበልጥ ይገለፅልሀል። ያያ ቱሪ ፣ ክሊች ፣ ዴቪድ አንቸሎቲ (የካርሎ አንቸሎቲ ልጅ) ላይሰንሳቸውን ለመውሰድ ይመጣሉ። በየጊዜው ኮርሶችን እየወሰዱ ከጊዜው ጋር መስተካከል ከሁሉም ይጠበቃል። ዕውቀቱ በየጊዜው መታደስ አለበት። ለምሳሌ እኔ B ላይሰንስ አለኝ ብዬ በየሁለት ዓመቱ ካላሻሻልኩት ኤክስፓይርድ ይሆንብኛል። ስለዚህ የግድ ዕውቀትን ማሻሻል ይጠይቃል። ከዚህ ከዚህ አንፃር ዕድሉን አግኝተው በዚህ ሀገር ደረጃ ቢማሩ የተሻሉ ተጫዋቾችን ማፍራት ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ሌላው ቢቀር በግንዛቤ ደረጃ ማደግ ይችላል።”
ከሚካኤል ጋር በነበረን ቆይታ ውስጥ በመጨረሻ የሰጠው ሀሳብ ለሀገር ውስጥ አሰልጣኞች በተለይም ለጀማሪዎች ጥሩ መልዕክት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
“ራስን ለማሻሻል የመጀመሪያው ነገር ማንበብ ነው ብዬ አስባለሁ። ፍላጎት ብቻውን ዋጋ የለውም ፤ የአሰልጣኝነት ወረቀቱንም ልታገኘው ትችላለህ ግን እሱን ማሻሻል የግድ ነው። አንድም በማንበብ ሁለትም ጨዋታዎችን በማየት እና በመተንተን። ጨዋታዎችን አይተህ ስትተነትን ግን የራስን ግምት ብቻ አይደለም ፤ ከሌላው አንፃርም ማመላከት ይጠይቃል። ያንተን ዕውቀት ከሌላው ጋር አስተያይተኸው ተጨማሪ ዕውቀት ስትጨምርበት የተሻለ ነው ፤ ማንበብ ግን የግድ ነው። ሌላው አሰልጣኝነትን በተግባር ማየት ያስፈልጋል። ወጥተው ማሰልጠን አለባቸው። በማሰልጠን ብቻ ከተጫዋቾች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማሻሻል አለባቸው። ብዙ በሰራህ ቁጥር ደግሞ ልምድ እያካበትክ ትሄዳለህ። ከዛም በላይ ጥቃቅን የሚባሉ ነገሮች ግልፅ እየሆኑልህ በራስ መተማመንህም እያደገ ይሄዳል። ሌላ ቦታ ላይ አሰልጥን ብትባልም አይከብድህም። ኮርሱ ብቻ ዋጋ የለውም ከኮርሱ በፊት ማንበብ ይቀድማል ብዬ አስባለሁ።”