ሀድያ ሆሳዕና የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

ነብሮቹ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የራምኬል ሎክንም ውል አራዝመዋል፡፡

ረዳት አሰልጣኝ በነበረው ያሬድ ገመቹ እንደሚመራ የሚጠበቀው ሀድያ ሆሳዕና በዛሬው ዕለት የሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የአንድ ነባር ተጫዋች ውልን አድሷል።

እንዳለ ደባልቄ በሁለት ዓመት ውል በይፋ አዲሱ የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋች ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና መለያ ላለፉት ዓመታት በመጫወት ቆይታ የነበረው የቀድሞው የደደቢት፣ ባህር ዳር ከተማ እና ጅማ አባጅፋር የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ከዚህ ቀደም ተጫውቶ ወዳሳለፈበት ሀድያ ሆሳዕና ዳግም መመለስ የቻለበትን ዝውውር አጠናቋል፡፡

አክሊሉ ዋለልኝም ሌላኛው የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ነው፡፡ ከሀዋሳ ወጣት ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ግልጋሎት የሰጠው እና በኢትዮጵያ ቡና ፣ ጅማ አባጅፋር ፣ ስሑል ሽረ እንዲሁም ወልዋሎ በአማካይ ስፍራ መጫወት የቻለው ተጫዋቹ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በሰበታ ጀምሮ በወልቂጤ መለያ ያጠናቀቀ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በአንድ ዓመት ውል መዳረሻውን ሀድያ ሆሳዕና አድርጓል፡፡

ከሁለቱ አዳዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ ክለቡ የአጥቂውን ራምኬል ሎክን ውል ለአንድ ዓመት አራዝሟል፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ድሬዳዋ እና ወልዋሎ ተጫዋች አርባምንጭ ከተማን በዓመቱ አጋማሽ ከለቀቀ በኋላ ያለፉትን ስድስት ወራት በቀይ እና ነጭ ለባሾቹ ቤት ማሳለፉ ይታወሳል፡፡