የሀዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ራሱን በገቢ ለማጠናከር “ክለባችን ኩራታችን” በሚል መሪ ቃል የሩጫ መርሐ-ግብር ሊያካሂድ ነው፡፡
በ1970 እንደተመሰረተ የሚነገርለት እና ከክልል ክለቦች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ሁለት ጊዜ በማንሳት በቀዳሚ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ በቀጣዩ የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ከወዲሁ ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን ክለቡም የፋይናንስ ችግሮች እንዳያጋጥሙት እና ከመንግሥት በጀት ራሱን ለማላቀቅ በርካታ የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች እንደጀመረ ተገልጿል።
ከእነዚህ የገቢ ማሰባሰብ ሂደቶች መካከል አንዱ የሆነው እና በርካቶችን ያሳትፋል ተብሎ የሚጠበቀው የሩጫ ውድድር ነሀሴ 28 2014 በከተማዋ ላይ ለማከናወን ስለ መታሰቡ ክለቡ ለዝግጅት ክፍላችን አስረድቷል፡፡ “ክለባችን ኩራታችን” በሚል መሪ ቃል ከተዘጋጀው የሩጫ መርሐ-ግብር ጋር ተያይዞ ሌሎች የገቢ ማሰባሰብ እና የክለቡን ታሪክ የሚያወሳ የዶክመንተሪ ፊልም እንደሚቀርብ እንዲሁም ተያያዥ ክንውኖች እንደሚኖሩም ጭምር አዘጋጅ ኮሚቴው ገልፆልናል።