ጎፈሬ ከደቡብ ሱዳኑ ክለብ ሙኑኪ ጋር ስምምነት ፈፀመ

የደቡብ ሱዳኑ ሻምፒዮን ሙኑኪ ክለብ ከሀገራችን የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ጋር የሦስት ዓመት ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል።

ግዙፉ ኢትዮጵያዊው የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ በሀገር ውስጥ ያለውን የስፖርት ጥያቄ ለመፍታት ከፍተኛ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ምህዳሩንም በማስፋት በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ምርቶቹን እያደረሰ ይገኛል። ከዚህ ቀደም ከደቡብ ሱዳኑ ማለኪያ ሶሻልና ባህላዊ ቡድን እንዲሁም ከዩጋንዳው ሞደርን ክለብ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ሦስተኛ ከኢትዮጵያ ውጪ ከሆነው የደቡብ ሱዳኑ ሙኑኪ ክለብ ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የጎፈሬ ዋና ቢሮ በተከናወነው የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ የተቋሙ መስራቾች አቶ ሳሙኤል መኮንን እና አቶ ሀሰን መሐመድ እንዲሁም የሙኑኪ ክለብ ዋና ፀሐፊ ጄምሰን ሴቢት ላዋቴ ተገኝተዋል። በቅድሚያ ሁለቱ አካላት ስምምነታቸውን በፊርማ ያፀኑ ሲሆን ከዛም በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት የትጥቅ ትውውቅ እና ርክክብ አከናውነዋል።

በማስከተል ስምምነቱን የተመለከተ ገለፃ መደረግ የተጀመረ ሲሆን መድረኩንም አቶ ሳሙኤል ወስደው ንግግራቸውን ማሰማት ጀምረዋል።”ስምምነቱ ለሦስት ዓመት ነው የሚቆየው። ክለቡ በየዓመቱ ከ7 ሺ እስከ 10 ሺ ድረስ የደጋፊዎች መለያ ይገዛናል ፤ እኛ ደግሞ የመጫወቻ መለያዎችን እና የልምምድ ትጥቆችን በነፃ የምናቀርብ ይሆናል። ጎፈሬ አሁን ዋና ዓላማው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ገበያ መቆጣጠር ነው። ሙኑኪ ከኢትዮጵያ ውጪ ሦስተኛ ክለባችን ይሆናል። ነገር ግን በዚህ አንቆምም ፤ እንቀጥላለን።

” ሙኑኪ ቻምፒዮን የሆነ ክለብ ነው። በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በባስኬት ቦል እና ቮሊ ቦልም ውጤታማ የሆነ ክለብ ነው። ቡድኖቹ ሻምፒዮን ስለሆኑም በአህጉራዊ ውድድሮች የእኛ ምርት የመተዋወቅ ዕድል ያገኛል። እንደገለፅኩት ስምምነቱ የሦስት ዓመት ስምምነት ነው። ሁሌ እንደምናደርገው የመጀመሪያው ዓመት መሰረት የመጣያ ነው። ከዛ በኋላ ያሉት ላይ ነው በደንብ ሥራዎች የሚሰሩት። ሙኑኪ ግን በጣም ብዙ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ስለሆነ ብዙ የደጋፊዎች መለያ ይወስዳል ብለን እናስባለን።” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በመቀጠል ደግሞ ሌላኛው የጎፈሬ ባለቤት ሀሰን መሐመድ “ጎፈሬ ከሀገር ውጪ እስካሁን በምስራቅ አፍሪካ ነው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው። እስካሁን ባለው ውጤታማ ሆነናል። ብራንዳችንም በጣም እየጨመረ ነው። ከዚህም ባሻገር ግን አሁን ላይ ከምዕራብ አፍሪካ ብዙ ፍላጎቶች እየመጡ ነው። በቅርቡም ወደዛ አካባቢ እንደምንሄድ ተስፋ አደርጋለው።”

ሚስተር ጄምሰን ሴቢት ላዋቴ በበኩላቸው ከጎፈሬ ጋር ባደረጉት ስምምነት ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው በቀጣይም ከሀገራቸው ደቡብ ሱዳን ሌሎች አራት ክለቦች ከጎፈሬ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ተናግረዋል። በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋርም የዳኞችን ትጥቅ ለማቅረብ ንግግሮች እየተጠናቀቁ እንደሆነ ጠቁመዋል።