በኢትዮጵያ ቡና ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫ ዙሪያ መግለጫ ተሰጥቷል

ትዮጵያ ቡና ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫ መርሐ ግብሩን እና ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

ዛሬ ከሰዓት አራት ኪሎ በሚገኘው አምባሳደር ሞል የኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም የክለቡ አጋሮች አመራሮች በተገኙበት የተለያዩ ጉዳዮች የተነሱበት መግለጫ የተሰጠ ሲሆን መግለጫውን የክለቡ ሥራ አስኪያኝ አቶ ገዛኸኝ ወልደ ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት ጀምረውት በመቀጠል በቦታው የተገኙ የሚዲያ አካላት ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ተሰጥቷል።

አቶ ገዛኸኝ ወልዴ መግለጫውን የጀመሩበት ንግግር እንደሚከተለው ይነበባል።

“ኢትዮጵያ ቡና ገቢውን የሚያገኘው ከቡናው ሴክተር ፣ ከስፖንሰሮቻችን እና ከደጋፊዎቻችን በተለያየ መንገድ በማስተባበር በምናገኘው ገንዘብ ነው። ክለቡ በዓመት ውስጥ እያስተዳደረ የሚገኘው ከዚህ አንፃር ባለፈው ቅዳሜ የከፈትነው የብራንድ ሾፕ ስላለ እሱንም የተገኙ ጋዜጠኞች እንዲያዩት ፣ እንዲጎበኙት እንዲሁም ደግሞ የቀረን ነገር ካለ ሀሳብ እንዲሰጡንም ጭምር ነው ዛሬ እዚህ ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲሰጥ በዋናነት የፈለግንበት ምክንያት። ስለዚህ አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያችን የክለቡ ብራንድ ሾፕ ወይንሞ ደግሞ በክለቡ ብራንድ የተለያዩ ዕቃዎችን በማቅረብ የክለቡን የገቢ አቅም ከፍ በማድረግ መስራት አለብን የሚለውን ይዘናል፡፡ ሁለተኛው ደጋፊዎቻችንን በተለያዩ ኤቨንቶች በማስተባበር በእነኚህም ውስጥ ደጋፊዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማድረግ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቦችን ማድረግ አለብን በሚል ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የያዝነው ተጨማሪ ስፖንሰሮችን ወደ ክለባችን በማምጣት የክለባችንን አቅም ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን መስራት የሚል ነው፡፡ ሌላው የያዝነው ምናልባት ሼር ካምፓኒው ውድድሩን በአዲስ አበባ ለማድረግ ዕቅድ አለው ይመስለኛል የመጨረሻው ውድድር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሚጠናቀቅ ከሆነ ጨዋታ በምናደርግበት ሰዓት የሜዳ ገቢያችንን ታሳቢ በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን መገኘት አለብን በማለት የጀማመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሚቀጥለው ዓመት ላይ ውድድሩ እንደ ተጀመረ አካባቢ ልናከናውናቸው ከሚገቡ ሥራዎች ውስጥ በዋናነት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዓመታዊ የቤተሰቦች ሩጫ ማከናወን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አራት ዙሮች የሩጫ ውድድሮችን አድርጓል፡፡ በዚህም ውስጥ አሰልጣኙም መልካም ተሞክሮዎች ፣ ሊያሻሽላቸው የሚገቡ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ እሱን ቀርፈን ተነጋግረን ፣ ተማምነን በሚቀጥለው ዓመት መስከረም 29 ላይ የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰቦች ዓመታዊ ሩጫ ይከናወናል ብለን ይዘናል፡፡ ይሄን ሩጫ ከዚህ በፊት ስናደርግ እንደነበረው ደጋፊዎቻችን በተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ነበር ትኬቶቻችንን ሲሸጡ የነበሩት ነገር ግን አሁን ይሄንን ሙሉ በሙሉ ቀይረነዋል፡፡ የትኬት ምዝገባዎችን የምናደርገው አንዱ ስፖንሰራችን በሆነው በቡና ባንክ አማካኝነት ይሆናል ማለት ነው። ምዝገባዎችንም የምናከናውነው ከነሀሴ 1 እስከ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ከነሀሴ 30 በኋላ ምዝገባዎችን አናከናውንም። ምክንያቱም ከነሀሴ 30 በኋላ የተመዘገበውን ደጋፊ ቁጥር ካወቅን በኋላ ወደ ህትመት መሄድ ስላለብን በተመዘገበው ደጋፊ ቁጥር ልክ ማሳተምም ስላለብን ነው። የቲሸርቱ የምዝገባ ዋጋ 500 ብር ነው ስለዚህ ደጋፊያችን በአምስት መቶ ብር እየተመዘገ ይቆያል እስከ ነሀሴ 30 ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ህትመት እንሄዳለን ማለት ነው ፤ በተመዘገበው ቁጥር ልክ፡፡ እኛ እስከ 50 ሺህ ደጋፊ ይሳተፋል ብለን ነው የያዝነው ፤ ከዚህም በላይ ሊሄድ ይችላል። ነገር ግን እኛ እስከ ሀምሳ ሺህ ቢሄድ በሚል ይዘናል ከዚህም በላይ ከሄደም ለማሳተም እንዲያስችለን ጊዜውን ሰፋ አድርገን ይዘናል፡፡ ሁለተኛው እና ልንሰራው ያሰብነው ጉዳይ ከስፖንሰራችን ሀበሻ ቢራ ጋር በመተባበር የዘንድሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅታችንን የምንጀምረው ነሀሴ 1 ላይ ነው በሀዋሳ ከተማ፡፡ ቅድመ ዝግጅት ከመጀመራችን በፊት ግን ተጫዋቾቻችን በአብዛኛው አዳዲሶች ናቸው ፤ አሰልጣኙም አዲስ ነው። አጠቃላይ ቡድኑን ለመላው ደጋፊ የማስተዋወቅ ሥራ እንሰራለን ብለን ይዘናል፡፡ ይሄንን አበበ ቢቂላ ስታዲየም ቅዳሜ ሐምሌ 30 መላው ደጋፊዎች በተገኘበት የመግቢያ ዋጋዎች አሉ ትኬቶች አሉ ስለዚህ ደጋፊው ገብቶ እያንዳንዱን ተጫዋች እንዲተዋወቅ ደጋፊውም ስሜቱ ምን እንደሆነ ለተጫዋቾቹ ምን ማስገንዘብ አለበት በሚል የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን። ይሄ አንዱ የገቢ ማሰባሰብ ስራችን አንዱ አካል ነው ማለት ይቻላል። በሚቀጥለው ዓመት ብዙ ገንዘብ ያስፈልገናል ብዙ ለመስራትም አስበናል ለተጫዋቾች ዝውውርም ብዙ ገንዘብ አውጥተናል። ይሄን መተካት የምንችለው እና ክለባችን ምንም እንዳይንገዳገድ በሚል ከደጋፊ ማህበር ጋር እየሰራን ነው፡፡”

በመቀጠል ከሚዲያ አካላት ለተነሱ ጥያቄዎች ተከታዮቹ ምላሾች ተሰጥተዋል።

የቡና ባንክ ተወካይ ስለሩጫ ውድድሩ…

“በቅድሚያ አርፍደን በመምጣታችን ይቅርታ እንጠይቃለን። ከዛ በመቀጠል እንግዲህ የቡና ስፖርት ክለብ እና የቡና ባንክ ባላቸው ግንኙነት በርካታ ሥራዎችን ሲሠሩ እንደነበር ይታወቃል። አሁንም በቅርብ በሚደረገው የዚህ ታላቅ ሩጫ ፕሮግራም ባንካችን የራሱን ዝግጅት ተዘጋጅቶ ጨርሷል። አዲስ አበባ ላይ ከ 170 በላይ ቅርንጫፎች አሉን እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጪ በመላ ሀገሪቱ ከ 365 በላይ ቅርንጫፎች ያለው ትልቅ ባንክ ነው። ሽያጮቻችንን እንግዲህ ከዚህ ቀደም የዛሬ ዓመት የነበረን ትልቅ ልምድ አለ ፤ ያንን ልምድ በመጠቀም ዘንድሮ እጅግ በጣም በተቀላጠፈ ሁኔታ የተገልጋዩን የደጋፊውን ጊዜ ፣ ጉልበት ፣ ሰዓት በጠበቀ መልኩ የሽያጭ መብት ለማከናወን ባንካችን ዝግጅት ማድረጉን በይፋ መናገር ይፈልጋል። አጠቃላይ ሁሉም ቅርጫፎቻችን እንዲሁም ደግሞ የዲጂታል ፕላትፎርማችንን ጨምሮ ሚፈለገውን ዓይነት የሽያጭ አገልግሎት በተፈለገው ሰዓት እና በሚሰጠው የጊዜ ገደብ በመተባበር ለመጨረስ ዝግጁነቱን መግለጽ ይፈልጋል። በድጋሚ በጋራ ትልቅ ውጤት እንደምናመጣ ተስፋ አለኝ ።”

ስለአሰልጣኝ ሹም ሽር እና ስለአቡበከር ናስር ዝውውር…

“በጣም ይቅርታ የተመቸ ጋዜጣዊ መግለጫ አይደለም ፤ ለዚህም በጣም ትልቅ ይቅርታ ነው ምንጠይቀው። ያው እኛ ሀሳባችን ሱቁ እዚህ ስላለ እንደው ጋዜጠኞችም ሱቁን አካባቢ እያዩ መግለጫ ብንሰጥ የተሻለ ይሆናል በሚል አስተሳሰብ እንደሆነ ተረዱልን። እና የማይመች ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም መጥታችሁ በዚህ መንገድ ጥያቄዎችን በማቅረባችሁ እጅግ አድርጌ አመሠግናለሁ። መጀመሪያ የተነሱት ላይ አሰልጣኝ ያው አሰልጣኝ በውጤቱ እየመዘንን ምንቀጥለው ስለሆነ በዛ መንገድ ነው ማየት ያለብን እንጂ ቁጥሩን ከቆጠርነው ማንችስተር ዩናይትድም በዓመት ውስጥ ስንት አሰልጣኝ ቀያይሯል ምናምን እያልን ልንደማምር ነው ማለት ነው። ዞሮ ዞሮ ግን ውጤት ለማምጣት ጥረት ማድረግ አለብን ብለን ነው 2015 ላይ የተነሳነው። በዛ መንገድ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን የሚል ነው። የአቡበከርን ዝውውር በተመለከተ በተለያየ መንገድ ለመግለጽ ሞክረናል። አንዳንድ ጊዜ ይፋ የማይደረጉ የዝውውር ሂደቶች አሉ ፤ በገንዘብ ደረጃ ማለት ነው። ስለዚህ እሱን ባለፈው በግልጽ በተለያዩ ሚዲያዎች ለማቅረብ ሞክሪያለሁ። በቂ ገንዘብ አግኝተናል የሚለው መልስ ነው። በቂ ገንዘብም ስላገኘን የተጫዋቾች ዝውውር ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርገናል የሚለውን በዛ ብመልሰው ይሻላል።”

ስለሩጫ ውድድሩ ስፖንስር…

“ከቡና ከጀርባ ያለው Back Logo ትክክል ነው። ግን ምንድነው ይሄ ሩጫው በዋናነት ስፖንሰር የሚደረገው በሀበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ነው። ለዛ ነው መግለጫውንም በዚህ ደረጃ ያደረግነው። ከሽያጩ ከምናገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ይሄንን ሩጫ በማድረጋችን ከሀበሻ ቢራ የምናገኘው ገንዘብ አለ። ስለዚህ ያንን ታሳቢ አድርገን የተዘጋጀ እንደሆነ ታሳቢ መደረግ አለበት።”

ስለስታዲየም ገቢ…

“የአዲስ አበባ ስታዲየምን በተመለከተ ከተባለው ክለብ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ) ጋራ ግንኙነት አላደረግንም። እንደዚህ ዓይነት ሀሳቦች በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነገሩ ሰምተናል። ጥሩ ሀሳብ ነው ይሄንን ሀሳብ በጋራ ተቀናጅቶ መጠየቅ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ግን አሁን ባለው ሁኔታ የአዲስ አበባ ስታዲየም ከሰኔ እስከ ሚቀጥለውም ዓመት መጠናቀቁ ጥያቄ የሚያስነሳ ይመስለኛል። ስለዚህ አዲስ አበባ ላይ ውድድር የማድረግ ዕድላችን በጣም እየጠበበ ነው የመጣው። በዚህ ምክንያት ደግሞ በዋናነት ከማንም በላይ ተጎጂ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ነው። ምክንያቱም ከሜዳ ገቢ ከፍተኛ ተጠቃሚ ከሆኑ ክለቦች የመጀመሪያ ረድፍ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ነው። ልክ በኮቪድ አማካኝነት ውድድሮች ሲቋረጡ 15 ውድድር አድርገን 16 ኛውን ጅማ ላይ ስናደርግ ነበር ተቋርጦ የነበረው እና በ15 ውድድሮች (አዲስአበባ ላይ በተደረጉት) 6.5 ሚሊዮን ብር ነበር ገቢያችን ያገኘነው ማለት ነው። 30ኛውን ጨዋታ ብንፈጽም እስከ 12.5 ሚሊዮን የሜዳ ገቢ ልናገኝ የምንችልበትና ይሄ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የበጀት እጥረታችንን ሊቀንስልን የሚችል እና በጀታችንን ከፍ ሊያደርግ የሚችል ነገር ነው እና ይሄን እያጣን ነው ያለነው። የፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒው ይሄን ነገር ትኩረት ይሠራበታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ግን የሱ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የስታዲየሙ ችግር ስለሆነ በዛ መንገድ እንዴት እንደምናደርገው አናውቅም። እንግዲህ ይሄንን ከነሱ ጋር መወያየት ይጠይቀናል። የአዲስ አበባ ስታዲየም የሚጠናቀቅ ከሆነ ግን እንደተባለው አዲስ አበባ ላይ በርከት እያልን ነው ክለቦች ስለዚህ በጋራ ሆነው የአዲስ አበባ ስታዲየምን በጋራ ልንጠቀምበት የምንችልበትን ዕድል መፍጠር አለብን። በነገራችን ላይ 2012 ከቫይረሱ መከሰት በፊት የነበሩትን ሂደቶች የአዲስ አበባ ስታዲየምን ራሳችን ነበርን ቲኬታችንን መቁረጥ የጀመርነው። ከፕሪሚየር ሊጉ ሼር ካምፓኒ ጋር ተነጋግረን ፣ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተነጋግረን እንዲሁም ባለቤቱ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ነበር። በወቅቱ የአሁኑ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከነሱ ጋር ተነጋግረን በራሳችን ነበር የምንቆርጠው። ኢትዮጵያ ቡናም የራሱን ይቆርጣል ቅዱስ ጊዮርጊስም የራሱን ይቆርጣል ለዛም ነበር በ15 ጨዋታ 6.5 ሚሊዮን ማስገባት የቻልነው። ራሳችን በመቁረጣችን ነበር ይሄ እንዲቀጥል አሁንም እንፈልጋለን አሁንም ይሳካል ወይ የሚለው በጣም ጨለምተኛም ባንሆን ብዙም ብርሃኑ ሚታይ አይደለም የሚል ነገር ነው ያለን።”

ለሽያጭ ስለሚቀርቡ ቲሸርቶች…

“ከቲሸርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ነገሮች አሁንም ደጋፊያችን እንዲገነዘብ ሚያስፈልጉት ነገሮች አሁን እኛ እያሳተምን ያለነው የክት ልብስ አይደለም። ዋናው ዓላማችን የገቢ ማሰባሰቢያ ነው አሁን ገቢ ነው ምንፈልገው። በከፍተኛ ሁኔታ ያው እንደምታውቁት የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ያለው የተጫዋቾች ዝውውር በዓመቱ ውስጥ 10,15,20 ፐርሰንት ይጨምራል ብለህ የምታስበው አይደለም 500 % ይጨምራል። ከዘንድሮው ደመወዝ የሚቀጥለው ደግሞ 500 % ሊጨምር ይችላል። ዘንድሮ 130 ሺህ ከሆነ የአንድ ትልቅ ደመወዝተኛ ተጫዋች 300 ሺህ ገብቶ ልታገኘው ትችላለህ። ስለዚህ በጣም በሚገርም ሁኔታ የሚጨምር ነው ፤ የተጠናም አይደለም። ጉዳዩ እና ይሄንን መሸፈን የግድ ይላል። ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል ደግሞ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ያስፈልጉናል ፤ ጥራት ያለው ቡድን መገንባት አለብን። ያንን ለማድረግ ደግሞ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል ምክንያቱም ታላቅ ክለብ ነው ሕዝባዊ መሠረት ያለው ክለብ ነው ስለዚህ ደጋፊዎች ወደ ገንዘብ መቀየር መቻል አለባቸው። ደጋፊዎች ይሄንን መረዳት መቻል አለባቸው አሁን ስለ ጥራት የምንጨነቅበት ጊዜ አይደለም። አሁን በዋናነት ፍላጎታችን ገቢ የማግኘት ጉዳይ ነው ገቢ ስናገኝ ግን በኤቨንቱ ላይ የክለቡን አርማ ፣ የክለቡን አጠቃላይ ቲሸርት ሊያመላክት የሚችል ቲሸርት ይኖረናል። ያ ቲሸርት ልክ ታላቁ ሩጫ እንደሚያደርገው በዛ ደረጃ የተቀረፀ ሊኖረን ይገባል። ከዛ ውጪ ግን ከዚህ በፊት እንደምናደርገው 500 ብር የሚያወጣ ቲሸርት ገዝተን 400 ብር የሚያወጣ ምዝገባ አድርገን ሩጫ አደረግን ለማለት ካልሆነ በስተቀር ገቢ ማግኘት ላይ ትኩረት አናደርግም ማለት ነው። በዋናነት አሁን ዓላማችን ገንዘብ ነው ፤ ገንዘብ ማግኘት አለብን። ስለዚህ ይሄንን ደግሞ ደጋፊያችን ይገነዘባል ብለን እናስባለን። ነገር ግን በተቻለ መጠን የዛሬ ሁለት ዓመት ይመስለኛል እንደተባለው ከስፌት ጋር ተያይዘው የነበሩ ችግሮችን በቀረፈ መንገድ እና ልክ ታላቁ ሩጫ በሚያደርገው መንገድ እኛም በዛ ሁኔታ እንሄዳለን ብለን ነው ታሳቢ እያደረግን ያለነው። ምስጋና ያነሳሃቸው ትክክል ናቸው። ሌሎችም ስፖንሰሮች እንዲሁ ብዙም የሚከፋን አይደለም። ይሄንንም ለመሥራት ደጋፊ ማኅበሩ በትኩረት የሚሠራበት ሁኔታ ይኖራል ብለን ታሳቢ እናደርጋለን።”

ስለአዲሱ የቡድኑ አሰልጣኝ

“ከአሰልጣኝ ጋር የተያያዘው ነገር ዞሮ ዞሮ በክለቡ ራዲዮ እና በክለቡ የማኅበራዊ ድረገፅ በይፋ የተገለፀ ስለሆነ በዛ መንገድ መቀጠሉ ይሻላል በሚል ነው ያደረግነው። ይፋዊ መግለጫም ከዚህ በኋላም አሰልጣኝ ቀጥረናል ብለን አሰልጣኝ ጋር ቁጭ ብለን ይፋዊ መግለጫ የምንሰጥበት ሂደትም የለም አሰልጣኙ ሥራውን ጀምሯል ፤ ወደ ሥራ ገብቷል። ስለዚህ ይፋዊም ተናግረናል ፤ ለተለያዩ ሚዲያዎች ፤ የሁለት ዓመታት ኮንትራት ሰጥተነዋል። በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ተስማምተናል። ከዛ ባሻገር ደግሞ በመጀመሪያው ዓመት ቡድኑ ለዋንጫ እንዲጫወት እና ዋንጫ ማምጣት የሚችል ቡድን እንዲሆን ተስማምተናል በዛ መንገድ እንቀጥላለን። ሌሎች የተለያዩ ሀሳቦች ካሉ ደግሞ እነ መንግሥቱ ሀሳብ ይሰጡበታል።”

ሊጉ አዲስ አበባ ላይ ያለመደረጉ ስለፈጠረው ችግር…

“አዲስ አበባ ላይ ውድድሮች አለመካሄዳቸው እኔ ከገንዘብ ጋር ብቻ እንዲገናኝ አልፈልግም። ከደጋፊው ስሜት ጋር ፤ አንዳንዴ ትውልድም እየገደልን ነው የሚል እሳቤ ነው ያለኝ። እና ሁላችንም ወደ ስታዲየም ስንመጣ የጀመርንበት ዕድሜ አለ ወደ ክፍለሃገር የወጣንበት ዕድሜም አለ ኳስ ለማየት እና የኢትዮጵያ ቡና በርካታ ደጋፊዎች በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኙ አሉ። ቤተሰቦቻቸው ይዘው መጥተው ጨዋታ ሚያሳይዋቸው በራሳቸውም ቢሆን በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ መጥተው እግርኳስን የሚያዩ በጣም ብዙ ወጣቶች አሉ። ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ይሄ ባለመደረጉ በቴሌቪዥን እና ከዛም በዘለለ በወሬ ብቻ ስለ ቡና እንዲከታተሉ ተደርጓል። እና ይሄ የምርት ጉዳይ ስለሆነ ከደጋፊ ማኅበሩ በኩል ጠንከር ብለን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቀዳሚነት ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮጀክቶችን የመጨረሽ ችግር የለም ሌላ አላማ እስከሌለው ድረስ ይሄን ስታዲየም ከተረባረብን ሚፈልገውን ፈንድ ሚመለከተው አካል ከመደበ ባጭር ጊዜ ውስጥ መጨረስ ይቻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ። በአጋጣሚ እኔ ቢሮዬ ስታዲየም አካባቢ ስለሆነ ካለሁበት ቢሮ ወደኋላ ስሄድ አየዋለሁ ሜዳው አካባቢ ያለው ነገር አልቋል ከሜዳ ውጪ ያሉ ሥራዎች ናቸው የቀሩት ስለዚህ በሦስት ወር እና በአራት ወር ሚሠራበት ቴክኖሎጂ ባለበት ጊዜ ላይ ይሄን ትውልድ ይሄን ደጋፊ ችግር ውስጥ መክተት ተገቢ አይደለም እና በዚህ አጋጣሚ የሚሰሙ ካሉ እንዲሰሙ እና ካልሆነ ግን በፎርማል ሁኔታ በዚህ ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ ውድድር እንዲደረግ የምንችለውን ሁሉ ጥረት እንደምናደርግ ለደጋፊው ለማሳሰብ ነው የምወደው።”

የጥሎ ማለፍ ውድድርን እንደ ተጨማሪ ገቢ ማግኛ…

“ይህን ሀሳብ በግሌ የምደግፈው ሀሳብ ነው። ፌዴሬሽኑ ሙሉ ለሙሉ ከሊግ ውድድሮች ወጥቶ እንደ እንግሊዙ ኤፍኤ ከታችኛው እርከን ጀምሮ የሚሳተፉ ቡድኖች የሚካፈሉበት የጥሎ ማለፍ ውድድር ወደ ማዘጋጀት መሸጋገር አለበት ፤ ከተቻለም የጥሎ ማለፉ አሸናፊ የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ የሚሳተፍበትን ዕድል መፍጠር ይኖርብናል። ከዚህ አንፃር ውድድሩ እንደተጨማሪ ገቢ የመፍጠርያ መንገድ ታቅዶ በቦታው ባሉ ሰዎች ይሰራል ብለን እንጠብቃለን። ውድድሩ ከጅምሩ ገንዘብ በሚያመነጭ መንገድ ባለመደራጀቱ በክለቦች ሀሳብ አቅራቢነት እንዲቀር ተደርጓል። ስለዚህ ውድድሩ ለአፍሪካ ተሳትፎ ከመደረግ ባለፈ ከነበረው ይዘት በተሻለ መልኩ ተደራጅቶ እንዲመለስ ጥረት እናደርጋለን።”

በክልል ከተደረጉ ጨዋታዎች ስለተገኘ ገቢ…

“በአዳማው ውድድር የተሻለ ገቢ አግኝተናል ፤ በንፅፅር ደግሞ በሀዋሳም የተሻለ ገቢ አግኝተናል። ከዚህ ውጭ ድሬዳዋ እና ባህር ዳር ላይ ግን ከአዲስ አበባ ትኬት እንዲቆርጡ የላክናቸውን ሰዎች አበል እንኳን የማይሸፍን ገቢ ነው ያገኘነው። ከቦታ ቦታ ያለውን ሁኔታ ማስተዳደር በራሱ በጣም ከባድ ነው። አክሲዮን ማህበሩ በሙሉ ሀላፊነቱን ለክለቦች ነው የሰጠው። ከዚህ ይልቅ ግን ይህ ሂደት በአንድ ማዕከል የሚመራበት መንገድ ቢፈጠር የተሻለ ይሆናል። ከፋይናንስ አንፃር ከተመለከትነው ውድድሩ አዲስ አበባ ላይ ባለመደረጉ በጣም ተጎድተናል። በዚህም ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ አጋጥሞናል። ለዚህም በአክሲዮን ማህበሩ ስብሰባ ላይ ሁሌም ሊጉ አዲስ አበባ ላይ የሚደረግበትን መንገድ ፈልጎ እያልን እየወተወትን ያለነው ቢያንስ ውድድሩ ለ5 ሳምንት እንኳን እዚህ ቢካሄድ እስከ 5 ሚልየን ብር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንችላለን ብለን እናምናለን። ነገርግን ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል።

“በቀጣይ ዓመት እንደስራ አመራር ቦርድ የወሰነው አንደኛው ጉዳይ በሊጉ የምናደርጋቸውን እያንዳንዱን ጨዋታ በተናጥል ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላትን እያፈላለግን እንገኛለን። በዚህ መንገድ ሰላሳውንም ጨዋታ በተናጥል ስፖንሰር የሚያደርጉ ተቋማትን ፕሮፖዛል ቀርፀን እያነጋገርን እንገኛለን። በዚህም ፈቀደኛ የሆኑ ተቋማትንም አግኝተናል። በዚህም ተቋማቱን በማህበራዊ ትስስር ገፆቻችን እና በራዲዮ ፕሮግራማችን ላይ የምናስተዋውቅ ይሆናል። በተጨማሪም በጨዋታ ወቅት ሜዳ ላይም አንድ የማስታወቂያ ሰሌዳም ቦታ እናመቻቻለን። በዚህም ከ30 ጨዋታ የተሻለ ገቢ ለመፍጠር አቅደናል።”

ስለሩጫው…

“የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰባዊ ሩጫ መስከረም 29 በመስቀል አደባባይ ይደረጋል ፤ ትኬቱም ከነሐሴ 1-30 በቡና ባንክ አማካኝነት የሚሸጥ ይሆናል። ሐምሌ 30 የቡድኑ አዳዲስ ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከጠዋቱ 3-5 ሰዓት የሚተዋወቁ ይሆናል።”