በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚደረገው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር የሚደረግበት ቀን ታውቋል፡፡
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር (ሴካፋ) ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ከ17 ዓመት በታች ቻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ እንደሚደረግ ከወር በፊት መገለፁ ይታወቃል፡፡ አዘጋጅ ሀገር ቀድሞው ይፋ መደረግ ቢችልም ውድድሩ የሚከወንበት ወር እና ቀን ሳይታወቅ የቆየ ሲሆን ሴካፋ በድረ-ገፁ ከሰዓታት በፊት ባወጣው መረጃ ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት 5 2015 ድረስ ለተከታታይ አስራ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
ከውድድሩ ቀደም ብሎ የዕጣ ማውጣቱ መርሐ-ግብር ከተደረገ በኋላ ሀገራት ከውድድሩ መጀመሪያ ቀን ቀደም ብለው ማለትም መስከረም 16 ላይ የዕድሜ ምርመራን (MRI) ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ማከናወን እንዳለባቸው ጨምሮ ገፁ አትቷል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ውድድር ላይ ቻምፒዮን መሆን የቻለ ቡድን በአልጄሪያ (አልጀርስ) በሚደረገው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡