ለሁለት ክለቦች በመፈረሙ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የሚገኘው ዊሊያም ሰለሞን ለሲዳማ ቡና ክለብ ጉዳዩን የተመለከተ ደብዳቤ በዛሬው ዕለት አስገብቷል፡፡
በየዓመቱ ተጫዋቾች ከአንድ ክለብ በላይ በመፈረም መነጋገሪያ ሲሆኑ መመልከት በሀገራችን እግር ኳስ ላይ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በዘንድሮ የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር ሂደት ላይ ተመሳሳይ የሆነ ድርጊትን አስተውለናል፡፡
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በጋራ ስምምነት መለያየት የቻለው አማካዩ ዊሊያም ሰለሞን ለአዳማ ከተማ እንዲሁም ለሲዳማ ቡና በመፈረሙ በሁለቱ ክለቦች መካከል የይገባኛል ጥያቄ ክርክር በመነሳቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዕልባት ለመስጠት ጉዳዩን እየመረመረ ይገኛል፡፡
በዚህ ሂደት መሀል ተጫዋቹ ለሚዲያ ተቋም “ለሲዳማ ቡና የፈረምኩት ተገድጄ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል ሲባል ቢሰማም ተጫዋቹ ግን ለየትኛውም የሚዲያ አካል ይሄን አላልኩም በማለት ለሲዳማ ቡና የይቅርታ እና እንዲሁም ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሚል ይዘት ያለውን ደብዳቤ ዛሬ ለክለቡ አስገብቷል፡፡
ተጫዋቹ በደብዳቤው እንዳሰፈረው “በዚህ ዓመት የዝውውር መስኮት ከክለባችሁ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ክለባችሁንም ሆነ አመራሩ ላይ ምንም ዓይነት ለሚዲያ ቀርቤ የተናገርኩት ሀሳብ ያለመኖሩን እየገለፅኩ ነገር ግን ሲዳማ ቡና
በእኔ ላይ የሚያነሳው ቅሬታ ካለ ለክለቡ እና ለክለቡ አመራር ይቅርታ እየጠየኩ የተፈጠረውን ችግር በስፖርታዊ መግባባት እንድንፈታው ስል በአክብሮት እጠይቃለሁ” በማለት የገለፀ ሲሆን ክለቡም በጉዳዩ ላይ በቀጣይ የሚሰጠው ምላሽ ይጠበቃል፡፡