በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክለው የቅዱስ ጊዮርጊስ የልዑክ ቡድን ነገ ወደ ታንዛንያ ጉዞ ያደርጋል።
የ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ ወር መጨረሻ ለሚኖረው የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ከሐምሌ 17 ጀምሮ በቢሸፍቱ ከተማ በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ በመከተም ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ሶከር ኢትዮጵያ ከሳምንት በፊት ፈረሰኞቹ ነሐሴ ወር መጨረሻ በአፍሪካ በቻምፒዮስ ሊጉ ለሚጠብቃቸው ጨዋታ ከታንዛኒያው ኃያል ክለብ ሲምባ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ባጋራነው መረጃ መሠረት ነገ ወደ ታንዛኒያ ያቀናሉ።
ነገ ወደ ታንዛኒያ በሚያቀናው ስብስብ ውስጥ ከተስፋ ቡድን ያደጉ ወጣት ተጫዋቾች ያልተካተቱ ሲሆን በቅርቡ ቡድኑን የተቀላቀሉት አዲስ ፈራሚዎችን ጨምሮ አብዛኛው ተጫዋቾች የጉዞ አካል መሆናቸውን ሰምተናል። በቤተሰብ ጉዳይ በአስራ አምስት ቀናት የቡድኑ ዝግጅት አካል ያልነበረው የወቅቱ የሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ እንደሚደርስ እና ነገ እንደሚጓዝ ከክለቡ አካባቢ ተነግሮናል።
ፈረሰኞቹ የአቋም መለኪያ ጨዋታቸውን የፊታችን ሰኞ አስር ሰዓት ላይ የሚያደርጉ ይሆናል።