በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው አማካዩ ሙሉቀን አዲሱ በትውልድ ሀገሩ አርሲ ነገሌ ለሚገኝ የፕሮጀክት ቡድን የቁሳቁስ ድጋፍን አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በመጫወት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች አሁን አሁን ወደ ተወለዱበት አካባቢ መለስ ብለው በልጅነት ላሳለፉባቸው እና በአካባቢያቸው ለሚገኙ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች ጎራ በማለት የትጥቅ ድጋፎችን ሲያደርጉ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ወደ ሲዳማ ቡና ማምራት የቻለው አማካዩ ሙሉቀን አዲሱ ተወልዶ ባደገበት አርሲ ነገሌ ከተማ ውስጥ ለሚገኝ የታዳጊ ፕሮጀክት የእግር ኳስ የስልጠና ማዕከል ድጋፍ አድርጓል፡፡
የቀድሞው የአርሲ ነገሌ ፣ ገላን ከተማ እና የተጠናቀቀውን ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ያሳለፈው የሲዳማ ቡናው አዲሱ ፈራሚ ማንያውቃል ለተባለ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት የትጥቅ ፣ የኮን እና የመጫወቻ ኳሶችን ድጋፍ ማድረጉን ለማወቅ ችለናል፡፡