ሀይቆቹ ዝግጅት የሚጀምሩበት ቀን ተረጋግጧል

በተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን አራተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማዎች የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን መቼ እንደሚጀምሩ ለሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ልከዋል።

በ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማዎች ለቀጣዩ የ2015 የሊጉ ውድድር ከአምናው በተለየ መልኩ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ በነቃ ሁኔታ በመሳተፍ የቅድመ ክንውን ስራዎችን ሲፈፅሙ ከርመዋል፡፡

ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ ቢሰጥም እዮብ አለማየሁ ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ ሙጂብ ቃሲም ፣ ሰይድ ሀሰን ፣ አዲሱ አቱላ ፣ ብርሃኑ አሻሞ ፣ ሰለሞን ወዴሳ እና ዓሊ ሱሌይማንን አዳዲስ ፈራሚ አድርጎ ውላቸው የተጠናቀቀውን መሀመድ ሙንታሪ ፣ ሀብታሙ መኮንን ፣ ቸርነት አውሽ እና ዳዊት ታደሰን ኮንትራት ለተጨማሪ ዓመት በማደስ መስከረም 20 2015 ለሚጀምረው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለማድረግ እየተሰናዳ ይገኛል።

በዚህም ነሀሴ 5 የክለቡ ተጫዋቾች ከተሰባሰቡ በኋላ በሁለት ቀናቶች ውስጥ የህክምና ምርመራ እና የሳይኮሎጂ ትምህርት እንዲያገኙ ተደርጎ ነሀሴ 8 በይፋ በክለቡ መቀመጫ ከተማ ሀዋሳ ዝግጅት የሚጀምሩ ይሆናል።