ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና የክልሎች ሻምፒዮና ነገ ይጀመራል

በሀዋሳ ከተማ አዘጋጅነት ከነገ ነሀሴ 1 ጀምሮ ለሚደረገው ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና የክልሎች ሻምፒዮና የዕጣ ማውጣት መርሀ – ግብር በዛሬው ዕለት ተከናውኗል፡፡

ከዚህ ቀደም ዓመቱን ሙሉ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በሚል መጠሪያ ይደረግ የነበረው ውድድር ካለፈው ዓመት ጀምሮ አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች ተማሪ ከመሆናቸው አንፃር በክረምት ትምህርት በሚዘጋበት ወቅት ውድድሩ መደረግ አለበት በሚል መከናወን የጀመረ ሲሆን የ2014 የውድድር ዘመንም በሀዋሳ ከተማ አዘጋጅነት ከነገ ነሀሴ 1 ጀምሮ መከናወን ይጀምራል፡፡

ክለቦችን እና ክልሎችን በተለያየ ምድብ ከፍሎ የሚደረገው ይህ ውድድር በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት የሚከናውን ሲሆን ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ የሚደረገው የዕጣ ማውጣት መርሀግብር በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ በዛሬው ዕለት ተከናውኖ የሚከተለው ድልድል ወጥቷል፡፡

በክልሎች ደረጃ (6)

ምድብ ሀ – ሀረሪ ክልል ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ አማራ ክልል
ምድብ ለ – ኦሮሚያ ክልል ፣ ቀይ ዛላ ( ሀላባ ደቡብ) ፣ ሲዳማ ክልል

በክለቦች ደረጃ (8)

ምድብ ሀ – ሀዋሳ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ባህርዳር ከነማ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ምድብ ለ – ወልቂጤ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ወላይታ ዲቻ ፣ አርባምንጭ ከተማ

ነገ በምድብ ሀ በክለቦች መካከል አዘጋጁ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ረፋድ 3፡00 ሰዓት በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ውድድሩ በይፋ ይጀመራል፡፡