ዐፄዎቹ ዝግጅታቸውን ነገ ይጀምራሉ

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው ፋሲል ከነማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ነገ በባህርዳር ከተማ ይጀምራል፡፡

በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ ሀለተኛ ላይ ተቀምጦ በማጠናቀቁ በ2022/23 የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፈው ፋሲል ከነማ በነሀሴ ወር መጨረሻ ለሚደረገው የአህጉሪቱ ሁለተኛ የክለቦች ውድድር ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ለመቅረብ እንዲሁም ደግሞ ለ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለሚያደርገው ተሳትፎ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር እየተሰናዳ ይገኛል።

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽን በዋና አሰልጣኝነት እስከ አሁን መሾሙን በይፋ ያላሳወቀው ክለቡ በለቀቃቸው ወሳኝ ተጫዋቾች ምትክ አዳዲስ አምስት ተጫዋቾችን በማስፈረም እና ነባር ሆነው ውላቸው ተጠናቆ የነበሩትን ደግሞ ውል በማደስ ላይ ያለፉትን ሳምንታት ተጠምዶ ከርሟል፡፡ በዚህም በአዲስ መልክ ሀብታሙ ገዛኸኝ ፣ ወንድማገኝ ማርቆስ ፣ ተስፋዬ ነጋሽ ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና መናፍ ዐወልን ያመጣው ቡድኑ ተጨማሪ ተጫዋቾችን በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ስብስቡ እንደሚቀላቅል የሚጠበቅ ሲሆን የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የሚያደርግበትን ቀን ይፋ አድርጓል።

ቡድኑ ከዛሬ ጀምሮ ለተጫዋቾቹ የህክምና ምርመራን ካደረገ በኋላ ነገ ሰኞ ነሀሴ 2 – 2014 በባህርዳር ከተማ በይፋ ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል፡፡