በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ የዊሊያም ሰለሞንን ዝውውር ጨምሮ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል፡፡
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን በዋና አሰልጣኝነት ከሾመ በኋላ በዝውውር ገበያው ለመሳተፍ ትንሽ የዘገየ የሚመስለው አዳማ ከተማ ከቀናት በፊት ለማስፈረም የተስማማቸውን የአምስት ተጫዋቾችን የዝውውር ሂደት ይፋ አድርጓል፡፡
ዊሊያም ሰለሞን በመጨረሻም የአዳማ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተገኘ በኋላ በመከላከያ እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና ቆይታ የነበረው አማካዩ ዊሊያም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ ለሲዳማ ቡና እና አዳማ በመፈረሙ በውዝግብ የተሞላ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በመጨረሻም ህጋዊ መልቀቂያ ለሰጠው አዳማ ውሉ ፀድቋል፡፡
መስዑድ መሐመድ ሁለተኛው የአዳማ ፈራሚ ሆኗል፡፡ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተገኘው እና በኢትዮጵያ ቡና ፣ በሰበታ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር መጫወት የቻለው አማካዩ ከብሔራዊ ቡድን የቻን ማጣሪያ ጨዋታ መልስ ለአዳማ ከተማ ፊርማውን አኑሯል፡፡
ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ሦስተኛ የክለቡ ፈራሚ ነው፡፡ የቀድሞው የጅማ አባጅፋር ፣ ወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ ከተማ ግብ ጠባቂ ከሳምንታት በፊት ለክለቡ የፈረመ ቢሆንም ክለቡ ዛሬ ዝውውሩን ይፋ አድርጓል፡፡
ዓመቱን ከሻሸመኔ ከተማ በውሰት በጅማ አባጅፋር ሁለተኛውን ዙር ያሳለፈው አጥቂው ቦና ዓሊ እና በተመሳሳይ በጅማ አባጅፋር በአማካይ ስፍራ የሚጫወተው አድናን ረሻድም የክለቡ ሌለኞቹ ፈራሚዎች ናቸው፡፡
ከአምስቱ ፈራሚዎች ባሻገር የመስመር ተከላካዩ ጀሚል ያዕቆብ በክለቡ ውሉ የተራዘመለት ተጫዋች ነው፡፡
ፎቶ : አድዬ የኔ ገፅ