ከ15 ዓመት በታች የታዳጊዎች ፓይለት ፕሮጀክት አሸናፊዎች ታውቀዋል

ለአስራ አምስት ቀናት በአርባምንጭ ከተማ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ከ15 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክት የምዘና ውድድር ተጠናቋል።

ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ እግርኳስ አስተናጋጅነት በሴቶች ዘጠኝ በወንዶች አስራ ሰባት ቡድኖችን አሳትፎ ሲካሄድ የቆየው ከአስራ አምስት ዓመት በታች የታዳጊዎች ፓይለት ፕሮጀክት የምዘና ውድድር በአስተናጋጇ ከተማ አርባምንጭ በርከት ያሉ ተመልካቾች በታደሙበት በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል። ዛሬ አስቀድሞ በተካሄደው የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ እና የድሬዳዋ የሴቶች ቡድንን ያገናኘው የፍፃሜ ጨዋታ ገና በጨዋታው መጀመርያ አንድ ደቂቃ ላይ በተቆጠረ ጎል አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጎሉም የዕለቱ ዳኛ የጨዋታው መጀመር እንዳበሰረች ከሰከንድ በኋላ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ፅዮን መሌ አፈትልካ በመውጣ በግብ ጠባቂዋ አናት ላይ ኳሱን በመላክ የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲን የመጀመርያ ጎል አስቆጥራለች። እንደ ጎሉ ፈጣንነት በቀሪው ደቂቃ ተጨማሪ ጎሎችን አስመልክቶን ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ቢባልም ዕምብዛም ሳቢ ሳይሆን ጨዋታው ሊቀጥል ችሏል። በቀጥተኛ አጨዋወት ጨዋታውን የጀመሩት የድሬ ዕንስቶች ወደ ፊት በሚጣሉ ኳሶች ጎል ጋር ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲዋ ግብ ጠባቂ ሀና በጋሸው ኳሱ ላይ ቀድማ በመገኘት ቡድኗ ጎል እንዳያስተናግድ በንቃት ስትጠብቅ ቆይታለች። ጨዋታውም በሁለቱም ቡድኖች ረጃጅም ኳሶች በዝቶበት የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ አሸናፊነት በመጠናቀቁ የውድድሩን ዋንጫ ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከፍ አድርገው አንስተዋል።

በመቀጠል አምስት ሰዓት ላይ የተካሄደው የወንዶች የፍፃሜ ጨዋታ በመደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ጎል ሳይቆጠርበት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምርት አምርቶ ድሬደዋ አርባምንጭን 5-4 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በሁለቱም የጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ አጨዋወት ካልተሳካ የጎል ሙከራ ጋር በተገባደደው በዚህ ጨዋታ በቀድሞ የአርባምንጭ ከተማ አማካይ በረከት ደሙ እየሰለጠኑ ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ ከዕድሜ ተገቢነት አንስቶ ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልባቸውን ታዳጊዎችን በመያዝ ጥሩ ቡድን መሆኑን ያስመለከተን የአርባምንጭ ኳሱን ተቆጣጥረው ጎሎችን ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት በድሬዎች ተከላካዮች ጥንካሬ ሳይሳካ ቀርቷል። በአንፃሩ ድሬዎች የአርባምንጭን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር በተሻጋሪ ኳስ ወደ ፊት ቢሄዱም የተሳካ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጠናቆ በመለያ ምት ድሬዳዋዎች 5-4 አሸናፊነት በመጠናቀቅ ውድድሩን በአንደኝነት በማጠናቀቅ የዋንጫ አሸናፊ ሆነዋል።