በቀጣዩ የሊጉ ውድድር ተጠናክሮ ለመቅረብ ቅድመ ስራዎችን ሲከውኑ የከረሙት አርባምንጭ ከተማዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምሩበት ቀን ይፋ ተደርጓል፡፡
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ መሪነት ከወረደበት ሊግ ዳግም የመሳተፍ ዕድልን አግኝቶ ለከርሞውም በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ተሳታፊ እንደሚሆን የታወቀው አርባምንጭ ከተማ አዩብ በቀታ ፣ ኢማኑኤል ላሪዬ ፣ ወንድማገኝ ኪራ ፣ አቤል ማሞ ፣ ተመስገን ደረሰ እና አካሉ አቲሞን አዳዲስ ፈራሚ ያደረገ ሲሆን ውላቸው ተገባዶ የነበሩ ነባር ተጫዋቾችን ኮንትራትም በማደስ ተጠምዶ ቆይቷል፡፡
ከአሁን በኋላ ምንም አዳዲስ ተጫዋቾችን እንደማይጨምር የሚጠበቀው ክለቡ የ2015 የውድድር ዘመን ቅድመ ዝግጅቱን መቼ ለማድረግ እንደወሰነ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
በዚህም መሠረት ቡድኑ ከነሀሴ 7 ጀምሮ በክለቡ መቀመጫ ከተማ አርባምንጭ ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል።