አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን በመቅጠር በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የሚጀመሩበት ቦታ እና ቀን ታውቋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሽርፍራፊ ደቂቃዎች መቆየቱን ያረጋገጠው ድሬዳዋ ከተማ ወጣቱን አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን ሳይጠበቅ የዋና አሰልጣኝነት ሚናን ከሰጠ በኋላ በዝውውር ገበያው በመሳተፍ ጫላ በንቲ ፣ ቢኒያም ጌታቸው ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ያሬድ ታደሰ ፣ እያሱ ለገሰ ፣ ኤልያስ አህመድ እና ዳንኤል ተሾመን ወደ ስብስባቸው በማካተት ውላቸው ተጠናቆ የነበሩ ነባር ተጫዋቾችን ውል በማራዘም ያለፉትን ሳምንታት አሳልፏል፡፡
በክለቡ ውል ካላቸው ተጫዋቾችም ጋር ከሰሞኑ በስምምነት እንደሚለያይ የሚጠበቀው እና ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በሂደት ላይ የሚገኘው የምስራቁ ክለብ ለ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሐሮማያ ከተማ ከነሀሴ 5 2014 ጀምሮ ለማድረግ እንደወሰነ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አሳውቋል፡፡