የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በቀጣዩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት እና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ዙርያ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ቀትር ላይ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ተካሂዷል።
በመግለጫው ላይ አክሲዮን ማህበሩን ወክለው የተገኙት የአክሲዮን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ ዓለቃ ፈቃደ ማሞ በቅድሚያ መግለጫው የተጠራበትን ዓላማ እና ዝርዝር ጉዳዮችን አስረድተዋል።
በመግቢያ ንግግራቸውም በሐምሌ 11 2014 የአክሲዮን ማህበሩ ቦርድ ባካሄደው መደበኛ ስብስባ ላይ ለህዝብ እና ሚዲያ መሆን ይገባቸዋል በተባሉ ጉዳዮች ላይ መግለጫ እንዲሰጥ በተወሰነው መሰረት ይህን መግለጫ ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም እሳቸው በስራ ምክንያት ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናታቸው መዘግየቱን አንስተው በዋነኝነትም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ምርጫ ላይ የአክሲዮን ማህበሩን ምልከታ ለማቅረብ እንደሆነ በማስረዳት ጀምረዋል።
በዝርዝር ሀሳባቸውንም በተከታዩ መልኩ አስረድተዋል
“በቅድሚያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ውስጥ የሚኖር ሰላም ሆነ ውጥረት በአጠቃላይ የአግር ኳሱ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል ይህም በብዙ መንገድ ይገለፃል ይህም ተፅዕኖ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አክሲዮን ማህበሩ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ለማሳያነትም ሱፐር ስፖርት ከዚህ ቀደም ይሰራባቸው ከነበሩት ሀገራት መካከል ኬኒያ አንዷ ነበረች ታድያ በክለቦች እና እግርኳሱን በሚመራው አካል መካከል የነበረው አለመግባባት በቀላሉ መፈታት አለመቻሉን ተከትሎ ራሱ ሱፐር ስፖርት እንኳን ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢያደርግም ይህ ችግር መፈታት ባለመቻሉ ሱፐር ስፖርት ኬንያን ለቆ ወጥቷል ፤ ይህ ሂደት በተመሳሳ በናይጄሪያ ማጋጠሙን ተከትሎ ናይጄሪያም ተመሳሳይ እጣ ደርሷታል። በመሆኑም ሱፐር ስፖርት ሁሌም ሰላም ባለበት ሀገር መስራትን ይመርጣል ስለዚህ እኛም ይህ ነገር እንዳይከሰት እንፈልጋለን።”
“በመሰረታዊነት በሦስት ጉዳዮች ላይ ለማተኮር እንፈልጋለን ፤ አንደኛው የፌደሬሽኑ የህንፃ ግዢ ጉዳይ ነው።ፊፋ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የራሱ ህንፃ እንዲኖረው ከአቶ ሳህሉ ገ/ወልድ በሀላፊነት ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ፤ የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚደንት ሴፕ ብላተር በአንድ ወቅት ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ ፌደሬሽኑ ከአዲስ አበባ ስታዲየም አቅራቢያ የራሱ ህንፃ እንዲገነባ የመሰረት ድንጋይ ጥለው ነበር ከዛ በኃላም ቦታው ወደ ገርጂ አካባቢ ተቀይሮም ቢሆን እውን ለማድረግ ተሞክሯል።በአቶ ጁነዲን ባሻ የስልጣን ጊዜም የተለያዩ ሙከራዎች ነበሩ ነገርግን ይህ ሂደት ሳይጠናቀቅ አቶ ኢሳያስ ጅራ ወደ ሀላፊነት መጥተዋል በሳቸው ዘመንም ይህን እውን ለማድረግ ኮሚቴ አዋቀረው ወደ ተግባር የገቡ ሲሆን ኮሚቴውም በቅድሚያ እንግሊዝ ኢምባሲ አካባቢ የሚገኝ አንድ ህንፃን ቢጠቁምም ቦታው በተወሰነ መልኩ ከመሀል ከተማ የራቀ ነው በሚል ውድቅ የተደረገ ሲሆን ቀጥሎም ይህ አሁን ፌደሬሽኑ የሚጠቀምበትን ህንፃ በ95ሚሊየን 450ሺህ ህንፃው እንዲገዛ ተደርጓል። ታድያ ይህ ህንፃ ከተገዛ አራት አመት ያስቆጠረ ቢሆንም እስካሁን ሻጩ ወገን ሊከፍለው የሚገባው ካፒታል ጌይን ታክስ (15%) እንዲሁም ገዢው ሊከፍለው የሚገባው አሹራ ታክስ (6%) ተከፍሎ የህንፃው የባለቤትነት ስም ወደ ፌደሬሽኑ መዞር ይገባ ነበር ነገርግን እነዚህ አራት አመታት ውስጥ ግን እስካሁን ስም አልዞረም ምክንያቱም ደግሞ ሻጩ አካል ይህን 15% አልከፈለም የገዛውም አካል ይህ እንዲከፈል ማድረግ ባለመቻሉ ነው። ስለዚህ ከህግ አንፃር ፌደሬሽኑ ህንፃውን ገዝቷል ማለት አንችልም ፤ በዚህም የተነሳ የህንፃው ተከራዮች ወደ ሀገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱበት ወቅት ከፌደሬሽኑ ጋር የተዋዋላችሁት ውል ልክ አይደለም እየተባሉ ይገኛል በዚህም ጉርምርምታ እየተፈጠረ ይገኛል። የእኛም ጥያቄ የባለቤትነት ጥያቄው መቼ ይፈታል ፤ ፌደሬሽኑን በበላይነት የሚከታተለው የመንግሥት አካልም ለምን ስም አላዞርክም ያለፉት አራት አመታት ኪራይስ ብሎ መጠየቅ ይገባዋል እንላለን።በፌደሬሽኑ በቀረበ የኦዲተር ኦዲት ሪፖርት ላይም በምክንያትነት የቀረበው ጉዳይ በመንግሦት ቢሮክራሲ ነው የሚል ቢሆንም መሰል ክፍያዎች ባልተፈፀሙበት እንዴት ሙሉ ክፍያ በአንድ ጊዜ ተፈፀመ የሚለው ጉዳይም መልስ የሚፈልግ ነው። በመሆኑም ይህ የተንከባለለ ችግር ወደ መጪው አስተዳደር መተላለፍ የለበትም እልባት ያስፈልገዋል።”
“ሁለተኛው ጉዳይ የትጥቅ ግዢን የሚመለከት ነው ፌደሬሽኑ ከኤሪያ ጋር በአቶ ጁነዲ ባሻ የስልጣን ዘመን ስምምነት መፈፀሙ ይታወሳል በዚህም ለዋልያዎቹ እና ለሉሲዎቹ በስፖንሰርነት ኤርያ እስከ 90,000 ዩሮ የሚያወጣ ትጥቅ እንደሚያቀርብ ፌደሬሽኑ ደግሞ ለእድሜ እርከን ቡድኖች ደግሞ እስከ 50,000 የሚያወጣ ትጥቅ ግዢ እንደሚፈፀም ተስማምተው ነበር። ታድያ በድንገት ምርቱ በገበያ እንደልብ አይገኝም እንዲሁም ጥራቱ የእኛን ፍላጎት አያረካም በሚል ከኤርያ ጋር የነበረው ስምምነት በፌደሬሽኑ ፍላጎት የተቋሙን ተጠሪ በማስጠራት እንዲቋረጥ ተደርጓል። በዚህም ጉዳዮ ወደ ጣሊያን ኢምባሲ ድረስ አምርቶ በውሉ መሰረት ፌደሬሽኑ 100,000ዩሮ እንዲከፍል የተወሰነበት ሲሆን በኃላ ላይ የተቋሙ ሰዎች ይህን ገንዘብ ሳይጠይቁ በመቅረታቸው ቀረ እንጂ ለትልቅ ኪሳራ ይዳርግ ነበር። ቀጥሎም በመስከረም 2011 ላይ ደግም ፌደሬሽኑ ኡምብሮ ከተሰኘ ተቋም ጋር ውል የገባ ሲሆን በዚህ ለአንድ ዓመት በሚዘልቀው ስምምነት ለዋናው የወንድ እና ሴት ብሔራዊ ቡድን በስፓንሰርሺፕ ትጥቅ በነፃ እንደሚያገኙ እንዲሁም ፌደሬሽኑ ደግሞ 12,500 የደጋፊዎች መለያን አንዱን በ2.50 ዶላር ሂሳብ ተርክቦ በመሸጥ ገንዘቡን ለኡምብሮ ገቢ እንደሚያደርግ ተገልፆ ነበር። በማርች 2021 ደግሞ ከተቋሙ ጋር ሌላ የግዢ ስምምነት የተፈፀመ ሲሆን በዚህም የ35,000 ዶላር የሚያወጣ የትጥቅ ግዢ እንዲሁም 12,500 የደጋፊ መለያ ለማቅረብ ነገርግን በአዲሱ ስምምነት የአንዱ የደጋፊ መለያ ዋጋ 8.50 ዶላር (ከቫት ውጭ) እንዲሆን እና ገንዘቡም ደግሞ ወዲያው እንዲከፈል ስምምነት ፈፀመዋል። በዚህ ሂደትም ይህ ሽያጭ እንዲፈፀም ለረዳ አንድ ኢትዮጵያዊ 200,000 ብር ያለአገባብ እንዲከፈል ተደርጓል ፤ እኔ እስከማውቀው በየትኛውም አሰራር ገዢ በየትም ዓለም ኮሚሽን አይከፍልም ኮሚሽን ቢኖር እንኳን ክፍያው የሚፈፀመው በሀገሪቱ ህግ ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ለሚገኝ ለተመዘገበ እና ህጋዊ ተቋም መሆን አለበት እንጂ ለግለሰብ ክፍያ መፈፀም የለበትም።”
“ሦስተኛው ጉዳይ ደግሞ ፌደሬሽኑ ለአንድ የስራ አስፈፃሚ አባል ለበዓል ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ 385,430 ብር ወጪ በማድረግ በቢዝነስ ክላስ የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት ተከፍሎ እንዲሄድ ተደርጓል።በየትኛውም ተቋማዊ አሰራር አንድ ግለሰብ ወደ ውጭ ሲላክ የሚሄድበት ስራ መታወቅ ይገባዋል በተጨማሪም ወደ ሀገር ሲመልስ ስለነበረው ቆይታ ሪፖርት ማድረግ ሲገባው ግለሰቡ እነዚህ ባልተደረጉበት ደርሶ እንዲመጣ ተደርጓል።ይህ ደግሞ ለብሔራዊ ቡድን እንኳን ለውድድር ገንዘብ የለኝም እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዮች ገንዘብ የለኝም ለሚል ተቋም በዚህ ደረጃ በግዴለሽነት ወጪ ማድረጉ የሚገርም ያደርገዋል።”
“እነዚህን አነሳን እንጂ ሌሎች ትንንሽ የሚመስሉ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም የኛንም ክብር የማይመጥን ስለሆኑ ወደ ጎን ትተን እነዚህ ነገሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ለምሳሌ በህንፃው ጉዳይ መንግሦት ጣልቃ ገብቶ እልባት መስጠት አለበት መሰል ችግሮች ተንከባለው መሄድ የለባቸውም ከሚል መነሻነት ይህን መግለጫ መስጠት አስፈልጎናል።”
በመቀጠልም በስፍራ ከታደሙ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች መቶ ዓለቃ ፈቃደ ምላሽ ሰጥተዋል ፤ ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ ትኩረት የሳቡት ሀሳቦች በተከታይ ቀርበዋል።
መግለጫው በዚህ ወቅት መደረጉ የምርጫ ቅስቀሳ ዓይነት ይዘት አለው…….
“መግለጫውን ማንም በፈለገው መንገድ መተርጎም ይችላል እኛ ግን የራሳችን ስጋት ስላለን ነው ይህን ያደረግነው ፤ ሦስቱ ተወዳዳሪዎች አሉ ይባላል የእነሱ ጉዳይ እኛን አይመለከተንም ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ነው።የአክሲዮን ማህበሩ መብት የተገደበ አይደለም ከፈለግን ወጥተን እከሌን በዚህ በዚህ መንገድ ይጠቅማል እና ምረጡ እከሌ ደግሞ በዚህ በዚህ ነገር አትምረጡ ማለት እንችላለን ነገርግን እኛ ይህን ማድረግ የፈለግነው ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚመጡት ሰዎች በማነለብኝነት ነገሮችን ከማድረግ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ለማድረግ ነው።”
-እነዚህ ስህተቶች ምንጫቸው ሙስና ወይስ በቸልተኝነት ወይም ባለማወቅ ነው ይላሉ?
“እኛ መደምደሚያ ላይ አልደረስንም ለምሳሌ አውሮፕላን ትኬት ገዝቶ መላኩ ምናልባት በግዴለሽነት እና ተጠያቂነት የለብንም ከሚል የመነጨ ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን የህንፃውን ጉዳይ ግን የመንግሦት ቢሮክራሲ በሚል ነበር ኦዲተር እስከቅርቡ ሪፖርት ያደረገው ፤ ታድያ በቅርቡ የተረዳነው የካፒታል ጌይን ታክስ መሆኑን ከተረዳን በኃላ በእምነት ሰውየው ይክፍላል በሚል ከሆነ ሪስክ ወስደሃል ትጠየቃለህ አይ ከዛ ውጭ ነው ብዬ ለመደምደም ይቸግረኛል።”
-ክለቦች ወደፊት በጋራ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ አንድ ድምፅ እንዲኖራቸው የማድረግ ውጥን አለ ወይ?
“የእኛ ተቋም በቅርቡ ነው ወደ እግር ኳሱ የመጣነው በዚህም ለሀገራችን እግርኳስ ይበጃል ያልነው እና ለእግርኳሳችን የሚሆነው አካሄድ የቱ ነው ብለን የተለያዩ አማራጮችን ገምግመናል ለአብነትም
የሰሜን አፍሪካ ሀገራት አካሄድ ውስብስብ እንደሆነ የምዕራብ አፍሪካውያንም እንዲሁ በሙስና የተጨማለቀ ነው በሚል በእኛ ምልከታ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ሆነን የደቡብ አፍሪካን ይበልጥ የተሻለው አማራጭ መሆኑን ተስማምተን ወደ ስፍራ አቅንተን እግርኳሱን ከምትመራው እንስት ጋር ሆነን በርከት ያሉ ጉዳዮችን አስረድተውን ለሁለታችንም የእነሱን መተዳደርያቸውን ሰጥተውን ነበር። መሆኑን ይህን ጥያቄ ጠይቀን ነበርን ነገርግን መልስ አላገኘንም ወደፊትም ለሚመጣውም አካል መጠየቃችንን እንቀጥላለን።”
-በምርጫው ዙርያ አክሲዮን ማህበሩ ስጋት አለው?
“እኛ ስጋት የለንም ፤ ለየትኛውም እጩ አናዳላም ምክንያቱም ይህን የሚወስነው ጠቅላላ ጉባኤው ስለሆነ ጠቅላላ ጉባኤውን ማሳመን እስከቻለ ማንም ይምጣ ማንም እኛ ችግር የለብንም።ማንም ቢመጣ ተግባብተን ለመስራት ዝግጁ ነን።”
-መረጃዎቹ በእጃችሁ ከነበሩ እስከአሁን መጠበቅ ለምን አስፈለገ?
“ትክክል ነው ፤ እኛ ግን ፕሬዘዳንት ስትመርጥ ሆነ የስራ አስፈፃሚ ስትመርጥ የእጩዎቹን የጀርባ ታሪክ መርምሩ ነው እያልን ያለው ምክንያቱ የሚመጣው ሰው የኛንም ሁኔታ ስለሚወስን ፤ የተሻለ ሰው የሚመጣ ከሆነ ሊጉን ይበልጥ እናሳድጋለን የተሳሳተ ከመጣ አሁንም ያለንን ልናጣ እንችላለን ከሚል ስጋት ነው።”
-መግለጫው በዚህ ጊዜ መሰጠቱ ከአቶ ከገዛኸኝ ወልዴ ጋር የሚያገናኘው ነገር ካለ?
“ከገዛኸኝ ጋር በኢትዮጵያ ቡና በአንድ አጋጣሚ ሰርተናል በመሆኑም እኔ አክሲዮን ማህበሩ ላይ ስላለሁ አትወዳደር ማለት አልችልም ይህ መብቱ ነው ፤ ከፈለገ ሀገሩን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት መወዳደር ይችላል ፤ ስለዚህ ገዛኸኝ ልወዳደር ካለ መብቱ ነው ምክር ከጠየቀኝ እሰጠዋለሁ ሌሎችም እጩ ሆነው ከመወዳደራቸው አስቀድመው ደውለው ሀሳቤን ጠይቀውኛል ለእነሱም ባለኝ ልምድ ይጠቅማል ያልኩትን አካፍያለሁ ወደፊት ከተመረጡ ፈቃደ ልክ ነው ሊሉኝ ይችሉ ይሆናል ፤ ነገር ግን መግለጫው ገዛኸኝን ለመጥቀም የተጠራ ነው የተባለው የአጭር ጊዜ እይታ ንግግር ነው።”
-ክለቦች በህጋዊነቱ ዙርያ ባወጡት ደብዳቤ መቃወማቸው ልዮነቶች በማህበሩ እና በክለቦች እየተፈጠረ ይሆናል
“16 ክለቦች አሉን ቦርድ አለን ፤ ለቦርዱ በቀረቡ ጉዳዮች ላይ በገለልተኝነት ተወያይተን መሰል ነገሮችን ለህዝቡ እና ሚዲያው አሳውቁ ተብሎ ተፈቅዶልናል ፤።እግርኳሱ ውስጥ የተበተነ አንድ ፍራቻ ተበትኗል በቃ ፈቃደ ወጥቶ ከተናገረ ሁላችንንም ያጠፋናል የሚል ሀሳብ አለ ለእኔ እኮ ትላንት በደብዳቤ እንደዚህ እንዳትናገር ብለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፅ/ቤት ሀላፊ የተፈረመ ደብዳቤ ልከውልኛል የፅ/ቤት ሀላፊው እንደ በዚህ በቅስቀሳ ወቅት ገለልተኛ መሆን ሲገባቸው ይህ ማድረጋቸው እጅግ ያሳፍራል።ግልፁን ለመናገር እኛ ጉዳዮን ይዘን እስከ ፊፋ ድረስ እንሄዳለን። ይህንን ነገሮችን ወደ አንድ ጥግ መውሰድ ለእግርኳሱ አይጠቅምም በህግ እንጠይቅሃለን ነው ያሉኝ ጠያቂ ካለ ለመጠየቅ ሆነ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ”
-ከአቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር ይህን ሂደት(ህንፃው) በተመለከተ ኢንፎልማሊ አውርታችኋል ወይ
“አዎ ተወያይተናል ። አቶ ኢሳያስ ጥሩ ሰው ናቸው እውነቴን ነው የምለው በማንኛውም ስብሰባ ተነጋግረን ሳንግባባ የወጣንበት የለም እሺ ብለው ይወጡ እና ነገሩ ግን ተግባራዊ ሲሆን ግን መመልከት አልቻልንም።”
-መጓተቱ ከቀጠለ እንደመፍትሄ የሚያቀርቡት ሀሳብ ካለ
“መፍትሄው መግባባት ከቻልን ቁጭ ብለን በችግሮቻችን ላይ ተወያይተን የፌደሬሽኑ ሆነ የፊፋ ህግ በሚፈቅደው መልኩ አዲስ ኮሚቴ ማዋቀር ነው ፤ እኛ መግባባት ካልቻልን ግን ፊፋ መፍትሄ ይሰጠናል። መፍትሔ የጠቅላላ ጉባኤ አባልት ቁጭ ብለው በመነጋገር መፍትሄ ማበጀት ነው ካልሆነ ግን ይህ አካሄድ ሀገራችን ለቅጣት እንዳይዳርግ እሰጋለሁ።”
-በምርጫ አስፈፃሚዎቹ ላይ የአክሲዮን ማህበሩ አቋም
“ይህን መመሪያ ከየት እንዳገኙት አላቅም ፤ እኔ በግሌ እንኳን ስለ እግርኳስ ፌደሬሽን ምርጫ ጠቅላይ ሚንስቴርም ሲመረጥ ሀሳብ በአደባባይ እንሰጥ የለም እንዴ ፤ ባለፈው ጠቅላላ ጉባኤ እንደተናገርኩት እጩዎች እዛው ጉባኤ ላይ ነበር የታጩት ነገርግን እንደ አካሄድ 30 ቀናት አስቀድሞ ታጭተው ለጠቅላላ ጉባኤ አባላት መበተን ነበረበት ባለመሆኑ ይህ ሁላ ችግር ተከስቷል። በመሰረታዊነት ግን እጩዎቹም አመራረጥ ጉዳይ ላይ በግሌ ባደረኩት ማጣራት እንደተረዳሁት ራሱ ፌደሬሽኑ እመራበታለው በሚለው የምርጫ ደንብ አንቀፅ 4 ንዑስ አንቀፅ 2 በሚደነግገው መሰረት የምርጫ አስፈፃሚ ሆነ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት በማንኛውም የፌደሬሽኑ አካላት ሆነ መንግስታዊ አመራርነት ላይ መሆን የለባቸውም ይላል። ግን ማን ተመረጠ ለምሳሌ የምርጫ አስፈፃሚው ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ሀይሉ ሞላ የፌደሬሽኑ የህግ አማካሪ እና ጠበቃ ናቸው ፣ መንግሥቱ ማሩ የዲሲፕልን ኮሚቴው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ናቸው ፣ በለጠ ዘወዴ – የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ እግርኳስ ቡድን ቡድን መሪ እና የጠቅላላ ጉባኤ አባል ፣ ረሂማ ዓወል – የድሬዳዋ ከተማ እግርኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈሚ ኮሚቴ አባል እና የጠቅላላ ጉባኤ አባል ናቸው ታድያ እነዚህን ነው ገለልተኛ ብለው የተመረጡት።ሁለተኛ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ላይ ቢያንስ ሊቀመንበሩ የህግ
እውቀት ሊኖረው ይገባል አቶ ብርሃኑ – ከዚህ ቀደም የሊግ ኮሚቴው ሊቀመንበር , አቶ አንበሳው የመንግሦት ባለስልጣን ናቸው ከላይ ያለውን መመሪያ ይጥሳል ሌላኛው አቶ ማሩ ናቸው ከእነዚህ አንዱም የህግ ባለሙያ አይደሉም። እነዚህ አካላት አንደኛ ፌደሬሽኑ ካወጣው ደንብ ጋር የሚጠረስ ሲሆን ሁለተኛው የፊፋን ህግ የሚጥስ ነው።ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱት አባላት ይህን ጥሰው የተመረጡ ናቸው።”