ከ15 ዓመት በታች የፓይለት ፕሮጀክት የምዘና ውድድር ምልከታዎች

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስተናጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ከ15 ዓመት በታች ታዳጊዎች የፓይለት ፕሮጀክቶች የሙከራ ውድድር ከቀናት በፊት በስኬት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ታድያ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ውድድር በወንዶች ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በሴቶች ደግሞ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲን አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል ፤ እኛም በዚህ ውድድር ላይ የተመለከትናቸውን የተወሰኑ ሀሳቦችን በዚህ ፅሁፍ ለመዳሰስ ሞክረናል።

ቀዳሚ የሆነው ጉዳይ የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ነው። መሰል የታዳጊዎች ውድድር በመሰረታዊነት ከማሸነፍ እና መሸነፍ ባለፈ የነገዎቹ የሀገሪቱ እግርኳስ ተረካቢዎች ያላቸውን አቅም የሚያሳዩበት መድረክ እንዲሆኑ ታልመው የሚዘጋጁ ናቸው። በዚህም መነሻነት በክለቦች ሆነ በሌሎች አካላት የምልመላ መረብ ውስጥ ገብተው የእግርኳስ መንገዳቸውን የተሻለ ለማድረግ የሚዘጋጁ ቢሆንም በሀገራችን ያለው እሳቤ ግን ከዚህ ያፈነገጠ ነው።

እግርኳስን በቅጡ ባልተረዱ አመራሮች እየተመራ በሚገኘው እግርኳሳችን ቡድኖች ወደ መሰል ውድድር ውስጥ ሲመጡ “ማሸነፍ ወይ ሞት” በሚል እሳቤ ውድድሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ፤ ከዚህም መካከል የተለመደው አካሄድ ከተቀመጠው የዕድሜ ጣርያ በላይ የሆኑ ተጫዋቾች ወደ ውድድር ማስገባት አንዱ ነው።

በመሆኑም የአርባምንጩ ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ እንደመደረጉ ትክክለኛውን ዕድሜ ይዞ በመቅረብ በወንዶች ተሸላሚ የሆኑት አርባምንጭ ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ፣ አማራ ወልድያ እና ጋምቤላ እንዲሁም በሴቶች ደግሞ ጋምቤላ ፣ሐረሪ፣ ሶማሌ፣ አዲስ አበባ፣ ኦሮምያ ፣ አጋሮ እና አሞ ከተማ ቡድኖች በተገቢው እድሜ የሚገኙ ታዳጊዎችን ይዘው በመቅረብ ተሸላሚ በመሆን ዕውቅና ማግኘታቸው መልካም ሆኖ ሳለ በግልፅ በሚታይ መልኩ ከዕድሜ በላይ የሆኑ ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ውድድሩ የመጡት ድሬዳዋ በሁለቱም ፆታ፣ አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ በሁለቱ ፆታ እንዲሁም ሲዳማ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በወንዶች በቀጣይ ራሳቸውን አርመው ከጊዜያዊ ውጤት ይልቅ የነገውን በማሰብ ትክክለኛ ታዳጊዎችን ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው እየገለፅን አወዳዳሪው አካልም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግበት እንደሚገባ ጥቆማችን ለማድረስ እንወዳለን።

ሌላው በውድድሩ የተመለከትነው እና ለወደፊት ዕርምት የሚሻው ጉዳይ ታዳጊዎቹን የሚያሰለጥኑት አሰልጣኞች ጉዳይ ነው። በታዳጊዎቹ እግርኳሳዊ ሆነ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትልቅ አስተዋፆኦ ያላቸው አሰልጣኞች ለተጫዋቾቻቸው አርዓያ መሆን ሲገባቸው የአንዳንዶቹ የጨዋታ ወቅት የሚያሳዩት ያልተገባ ስነምግባር እጅግ አሳፋሪ ሆኖ አግኝተነዋል። ይህም ድርጊታቸው በስራቸው በሚገኙት ታዳጊዎች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅእኖ ቀላል ባለመሆኑ ይህ ጉዳይ እርምት ሊደረግበት ይገባል እንላለን። በተለይ በመዝጊያው መርሐ ግብር ላይ የድሬዳዋ የወንዶች ቡድን አሰልጣኝ የሆነው አካዳሚ ከበደ ኮከብ አሰልጣኝ መሆን ይገባኛል በማለት ያሳዮት ያልተገባ ባህሪ እጅግ መስተካከል ያለበት መሆኑን እንገልፃለን።

በውድድሩ በዋነኝነት የተመለከትነው አውንታዊ ጉዳይ በወንዶች እግርኳስ ጋምቤላ ፣ ሻሸመኔ ፣ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ ጅማ ፣ አርባምንጭ ቡድኖች ይዘዋቸው የመጡት በትክክለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች እንዳለ ሆኖ በቀጣይነት ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራባቸው በመጪዎቹ ዘመናት የኢትዮጵያ እግርኳስን ሊቆጣጠሩ የሚችሉ ተስፈኛ ታዳጊዎችን ተመልክተናል።

እነዚህ ነገ እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድረስ መዝለቅ የሚችሉ ተስፈኛ ታዳጊዎችን አንድ ጊዜ ታይተው ብቻ እንዳይመጡ በመጡባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ከቤተሰብ አንስቶ እግርኳሱ የሚመሩ አካላት ጭምር ለእነዚህ ታዳጊዎች የዕለት ከዕለት ትኩረት በመስጠት ዕገዛ ሊያደርጉላችው እንደሚገባ መልዕክታችን ነው።

በውድድሩ ተስፈኛ ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን ተስፈኛ ዳኞችን እንዲሁ ተመልክተናል። በአርባምንጩ ውድድር ላይ በርከት ያሉ የጨዋታውን ህግ ጠንቅቀው የተረዱ ቆራጥ ዳኞችን እንዲሁ ያስመለከተን ውድድር ነበር። ምንም እንኳን የታዳጊዎች ውድድር ቢሆንም በዳኝነቱ ረገድ የተመለከትነው ተስፋ ሰጪ ሂደት በቀጣይ በከፍተኛ ደረጃ መዳኘት የሚችሉ ጥሩ ጥሩ ተተኪ ዳኞችም እንዳሉን ያረጋገጠ ውድድር ነበር።

በመጨረሻም በአርባምንጭ የተደረገው ውድድር ከፍተኛ ቁጥር ባለው ደጋፊ ታጅቦ የተደረገ ነበር ፤ በጨዋታ ዕለት የነበረውን የተመልካች ብዛት ላስተዋለ ውድድሩ በከፍተኛ ደረጃ የሚደረግ የክለቦች የፉክክር ጨዋታን ለመመልከት እንጂ የታዳጊዎችን ጨዋታ ለመከታተል በፍፁም አይመስልም ነበር።

ለወትሮም ቢሆን ለእግርኳስ ባለው ፍቅር የማይታማው የአርባምንጭ እና አካባቢ ነዋሪ እነዚህ ታዳጊዎችን ለማበረታታት በከፍተኛ ቁጥር ወደ ስታዲየም ሲተም ተመልክተናል ፤ ከዚህም ባለፈ ውድድሩ የተደረገበት የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብም እንዲሁ በነቂስ ውድድሩን ሲከታተል አስተውለናል።

ይህም የከተማ ሆነ የዞኑ አስተዳደሩ በአካባቢው የሚስተዋለውን መሰረታዊ የሆነ የመሰረተ ልማት ችግር በመቅረፍ ሌሎች የክለቦች ውድድሮችን ወደ ከተማው በማምጣት ፈርጀ ብዙ ጥቅሞችን ሊያገኝበት ስለሚችልበት መንገድ ማጤን ይገባዋል እንላለን።

ከሞላ ጎደል የአርባምንጩ ውድድር ስኬታማ የነበረ ሲሆን ይህን ውድድር በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ያሉበትን ውስንነቶች በመቅረፍ የተሻለ ውድድር ለማድረግ ሁሉም አካላት በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል የሚለው ጉዳይ የማሳረጊያ ነጥባችን ነው።

በውድድሩ ላይ ትኩረታችንን የሳቡ ተስፈኛ ታዳጊዎች

ግብ ጠባቂ – በረከት ማርቆስ (አዲስ አበባ) ምህረት አበበ (ድሬዳዋ)

ተከላካይ – ቤቢ ከድር (አርባምንጭ) ፣ ዳዊት ተሾመ(አአ) ፣ ሰኢድ ከድር (ሻሸመኔ) ፣ ቢንያም ደረጄ (አዲስ አበባ) ፣ አማኑኤል አብርሃም (አዲስ አበባ)

አማካይ – እንድርያስ ተፈሪ (አዲስ አበባ) ፣ በረከት ዲፋዬ (አርባምንጭ) ፣ አንሙት ደለልከኝ (አርባምንጭ) ፣ ናዝራዊ ማትዮስ (አርባምንጭ)

አጥቂ – እንየው ስለሺ (አርባምንጭ) ፣ ዮሐንስ ተስፋዬ (ባህር ዳር) ፣ ሙንተሊን ተይሳል (አዲስ አበባ) ፋሲካ መላኩ (ጅማ) ፣ ናትናኤል ፍቅሬ(ጅማ) ኦዶ መሐመድ (ሻሸመኔ)

በሴቶች

ረቂቅ አሰፋ (ሲዳማ)
ፅዮን ገበየሁ ( አርባምንጭ)
እየሩሳሌም ምኞት (አርባምንጭ)