ሀድያ ሆሳዕና የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሆሳዕና ከተማ የሚጀምርበትን ቀን ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡
ከአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጋር ያለውን ጉዳይ እስከ አሁን ያልቋጨው ሀድያ ሆሳዕና የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በረዳት አሰልጣኙ ያሬድ ገመቹ መሪነት ለመጀመር ቀን ቆርጧል፡፡ ክለቡ ቤዛ መድህን ፣ ዳግም ንጉሴ፣ ሰመረ ሀፍታይ ፣ እንዳለ ደባልቄ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ዘካሪያስ ፍቅሬን ወደ ስብስቡ መቀላቀል ቢችልም ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የአንዱንም ዝውውር አላፀደቀም። በያዝነው ሳምንት ደግሞ ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማምጣት በሂደት ላይ እንደሚገኝ አውቀናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ክለቡ ዝግጅት የሚጀምርበትን ቀን ግን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህም ከነሀሴ 7 ጀምሮ ለቡድኑ አጠቃላይ አባላት የቅድመ ህክምና ምርመራን ከከወነ በኋላ ነሀሴ 9 የቀጣይ ዓመት ዝግጅቱን በክለቡ መቀመጫ ከተማ በሆነችው ሆሳዕና በይፋ ይጀምራል፡፡