የአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ምክትል ታውቀዋል

መቻልን ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ለማሰልጠን ፊርማቸውን ያኖሩት አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የቀድሞ ምክትል አሠልጣኛቸውን ዳግም አግኝተዋል።

የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባህር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ አሠልጣኝ የነበሩት ፋሲል ተካልኝ በቀጣዩ ዓመት በተጫዋችነት ያሳለፉበትን መቻል በአሠልጣኝነት ለማገልገል ፊርማ አኑረው የተለያዩ ተጫዋቾችን እያዘዋወሩ እንደሚገኝ ይታወቃል። አሠልጣኙ መንበራቸውን ከያዙ በኋላ ምክትል አሠልጣኝ በምርጫቸው እንዲያመጡ በክለቡ ነፃነት ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የቀድሞ አጋራቸውን በምክትልነት መሾማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በዚህም አሠልጣኝ ታደሠ ጥላሁን የክለቡ ምክትል አሠልጣኝ ሆነዋል። የቀድሞ የሱሉልታ ከተማ፣ ሜታ ቢራ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ኢኮስኮ አሠልጣኝ በፕሪምየር ሊጉ ከፋሲል ተካልኝ ጋር በባህር ዳር ከተማ ቤት በጋራ መስራታቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ በአንድ ዓመት ውል ወደ መቻል ማምራታቸው እርግጥ ሆኗል።

መቻል ከዚህ ቀደም የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኙ በለጠ ወዳጆን ውልም ማደሱ አይዘነጋም።

ያጋሩ