ባህርዳር ከተማ የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቼ እና የት እንደሚጀምር ተገልጿል።
በተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በሊጉ ለመቆየት ሲታትሩ ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ የነበረው ባህርዳር ከተማ ለቀጣዩ ዓመት በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ መሪነት በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ በንቃት ሲሳተፉ የተመለከትን ሲሆን ከአሁን በኋላ እንደሚፈፅሙ ከሚጠበቁ ጥቂት ዝውውሮች ውጪ ያሬድ ባዬ ፣ የአብስራ ተስፋዬ ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ ፣ ቻርለስ ሪባኑ ፣ ሀብታሙ ታደሰ ፣ ተስፋዬ ታምራት ፣ ፍፁም ጥላሁን እና ፍራኦል መንግስቱን የቡድኑ አካል ማድረግ ችሏል። ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች በተጨማሪ ውላቸው የተጠናቀቁ ወሳኝ የቡድኑ ተጫዋቾችንም ኮንትራት በማደስ የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር ለተጫዋቾቹ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ክለቡ ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ ለተጫዋቾቹ የህክምና ምርመራ እና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን ካገባደደ በኋላ ዕለተ ሰኞ ነሀሴ 9 በመቀመጫ ከተማው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚጀምር ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ይፋ አድርጓል፡፡