“ንግድ ባንክ የመጣሁበት ዋነኛ ዓላማዬ ዋንጫ ለማንሳትና ታሪክ ለመስራት ነው”

አዲሷ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋች መሳይ ተመስገን በሴካፋ የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር እና ዝግጅት ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ከዓምና ጀምሮ የእንስቶች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድርን ማዘጋጀት እንደጀመረ ይታወቃል። በአህጉሩ በሚገኙ ስድስት ቀጠናዎች የማጣሪያ ውድድሮች ተከናውነው አሸናፊዎቹን የሚያሳትፈው ትልቁ የሴት ክለቦች ውድድር ዘንድሮ በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚደረግ ሲሆን የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ፍልሚያም በሳምንቱ መጨረሻ በታንዛኒያ ይጀመራል። በመድረኩ ሀገራችንን የሚወክለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ትናንት ረፋድ ወደ ስፍራው ያቀና ሲሆን ዛሬ ቀትር ላይም የመጀመሪያ ልምምዱን በኡሁሩ ስታዲየም እንዳከናወነ መረጃ አጋርተናችሁ ነበር።

ለውድድሩ 20 ተጫዋቾችን ይዞ ያቀናው ንግድ ባንክ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን የፊታችን ሰኞ 7 ሰዓት ከዛንዚባሩ ዋሪየርስ ኩዊንስ ጋር የሚያደርግ ይሆናል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እንደተገባደደ ወዲያው 6 ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለው ቡድኑ (ንቦኝ የን እና ቅድስት ዘለቀ ግን በቅደም ተከተል ከውል እና ከቤተሰብ ችግር ጋር በተገናኘ ስብስቡን አልተቀላቀሉም) በጥሩ መንፈስ ልምምዱን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ቡድኑን ከተቀላቀሉ አዲስ ተጫዋቾች መካከል ከመሳይ ተመስገን ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተገኘችው መሳይ 2011 እና 12 በኢትዮ ኤሌክትሪክ ያሳለፈች ሲሆን ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በመከላከያ የእግር ኳስ ህይወቷን ቀጥላለች። ቻምፒዮኖቹን የተቀላቀለችው ተጫዋቿም ስለ አዲሱ ክለቧ፣ ስለሴካፋ ውድድር ዝግጅት እና ማሳካት ስለምትፈልጋቸው ሀሳቦች ያነሳችበትን አጠር ያለ ቆይታ እነሆ!

አዲሱ ክለብሽን እንዴት አገኘሽው?

“አዲሱ ክለቤ ጥሩ ነው። በክለቡም ደስተኛ ነኝ። ከልምምድ ጀምሮ ያለው ነገር ተመችቶኛል። ተጫዋቾቹም ጋር ያለው ነገር ጥሩ ነው። የቡድን መንፈሱ እኔ ከነበርኩበት ቡድን የተሻለ ነው።”

በአጭር ጊዜ ልምምድ ነው ከቡድኑ ጋር ወደ ታንዛኒያ ያቀናሽው ፤ ከቡድኑ ጋር ምን ያህል ተዋህጃለው ብለሽ ታስቢያለሽ?

“ልክ ነው ፤ ቡድኑን በቅርብ ነው የተቀላቀልኩት። ለውድድሩ ጠንካራ ዝግጅት ነው እየሰራን ያለነው። ከውድድር ስለመጣን ያን ያህል የማች ፊትነስ ጥያቄ የለብንም። አሠልጣኛችንም ከውድድር መምጣታችንን ታሳቢ አድርጎ መካከለኛ የሚባል ግን አስፈላጊ ልምምዶችን እየሰጠን ነው። በአጠቃላይ ባለችው ጊዜ ከተጫዋቾቹ ጋር በጥሩ ሁኔታ እየተዋሀድን ነው ብዬ አስባለው። ከፈጣሪ ጋርም ጥሩ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለው።”

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዋክብት የሚገኙበት ክለብ ነው። በቡድኑ ውስጥ በቋሚነት ለመሰለፍ ትንሽ ከፍ ያለ ፉክክርን ማለፍ ይጠይቃል። ለዚህ ፈተና ራስሽን በምን ያህል ደረጃ እያዘጋጀሽ ነው?

“እውነት ነው ፤ ንግድ ባንክ የጥሩ ተጫዋቾች ስብስብ ክለብ ነው። እኔም ደግሞ የዚህ ስብስብ አንዷ አካል ነኝ። ይሄንን ስል ግን ሥራ አይጠብቀኝም እያልኩ አይደለም። ሥራ ይጠይቃል። ስለአሰላለፍ ምናምን አሁን ማንሳት አልፈልግም። እርሱ የአሠልጣኝ ጉዳይ ነው። ይሄንን ለእርሱ ትቼ እኔ ግን አሠልጣኙ በሚሰጠው ልምምድ ላይ ብቁ ሆኜ ለመገኘት እሞክራለው። አሰላለፉም የሚወጣው በሥራችን ነው። አሰላለፍ ሥራችንን ነው የሚገልፀው።”

የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር ዋንጫ ሲያነሳ የስብስቡ አባል ነበርሽ፣ ዋናው ብሔራዊ ቡድንም በዚሁ የቀጠና ውድድር ጥሩ ግስጋሴ ሲያደርግም እንደዛው ፤ አሁን ደግሞ ለሌላኛው የዞኑ የክለቦች ውድድር ወደ ታንዛኒያ አምርተሻል። በዚህ ውድድር ለንግድ ባንክ ምን አይነት ጭማሪ እሰጣለው ብለሽ ታስቢያለሽ?

“በብሔራዊ ቡድን ደረጃ እንደተባለው ደረጃ በደረጃ ጥሩ ስኬት አስመዝግቤያለው። በእድሜ ቡድኑ ዋንጫ ይዘን መጥተናል። በዋናው ቡድን ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዘን አጠናቀናል። እርግጥ ከሀገር ውጪ የሚገኙ ቡድኖች ትንሽ ፈተን ያደርጉናል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ይህንን ፈተና ተቋቁመን ውጤት አምጥተናል። ንግድ ባንክ ደግሞ ለአፍሪካ ክለቦች ያንሳል ብዬ አላስብም ፤ ሁሉም ተጫዋች ልምድ ያለው ነው። ትንሽም ቢሆን ሁላችንም ልምምድ አለን። እኔም አይቼዋለው። ስለዚህ አዲስ አይሆንብኝም። እኔም ተጨምሬበት ተጫዋቾቹ ላይ ከማየው አቅም መነሻነት ዋንጫ ይዘን እንደምንመጣ ነው የማስበው።”

ከዓምና ጀምሮ ያለ እረፍት በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለብ ደረጃ ብዙ ጨዋታዎችን ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል አንቺ አንዷ ነሽ። አሁንም የሊጉ ጨዋታዎች እንዳለቁ ወደ ሌላ ውድድር ያለ እረፍት እያመራሽ ነው። ይሄንን ነገር እንዴት እያስተናገድሽው ነው?

“ልክ ነው ፤ ብዙ ውድድሮች ተደራርበዋል። ውድድሮች መብዛታቸው ግን ያጠነክረኛል እንጂ አያደክመኝም። አሁን የማርፍበት ጊዜ አይደለም። የሚገኙ ዕድሎችን ደስተኛ ሆኜ ነው የምጠቀማቸው። እኔ ብሔራዊ ቡድን በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ። በሊጉም ጥሩ ነገር በማሳየቴ ደስተኛ ነኝ። አሁን ንግድ ባንክ ስመጣም ደከመኝ ማለት አልፈልግም። ለሌላ አዲስ ታሪክ ነው የመጣሁት። እኔ በክለብ ደረጃ ታሪክ የለኝም ፤ ደረጃ መውጣት ብቻ ይሆናል ያለኝ ታሪክ። አሁን ንግድ ባንክ የመጣሁበት ዋነኛ ዓላማዬ ዋንጫ ለማንሳትና ታሪክ ለመስራት ነው። በአጠቃላይ በሁሉም ነገሮች ደስተኛ ነኝ። ፈተና ያጠነክራል እንጂ አይጥልም ብዬ አስባለው።”

ታንዛኒያ ገብታችኋል ፤ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታችሁንም ሰኞ ታከናውናላችሁ። በውድድሩ እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ግል የታሰበውን ነገር አጋሪኝ እስቲ…?

“እቅዳችን አንድ እና አንድ ነው። እቅዳችን ዋንጫ ይዞ መምጣት ነው። ዋንጫ ይዞ ለመምጣት የሚያስችል አቅም ደግሞ አለን። አቅም መኖር ብቻ ግን ትርጉም የለውም። አውጥተን መጠቀም አለብን። እርግጥ እግር ኳስ የዕለት ብቃት የሚወስነው ነገር ነው ፤ እንዲህ ቃልም አይገባበትም። ግን የምንችለውን ካደረግን ዋንጫ የማናመጣበት ምክንያት የለም። እኔ ደግሞ በግሌ የተሻለ ነገር ለማድረግ የአቅሜን ሁሉ ለንግድ ባንክ እሰጣለው።”

በመጨረሻ…?

“የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ነገር ከእኛ ይጠብቃል ፤ ምክንያቱም ህዝብን ወክለን ስለሆነ የምንሄደው። ከእግዚአብሔር ጋር አናሳፍራችሁም ማለት እፈልጋለው።”