የቀድሞው ስያሜውን ያገኘው መቻል የዝግጅት ቀኑ ታውቋል

በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ የቀላቀለው መቻል በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቼ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመለሱት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጋር እንደማይቀጥል ከገለፀ በኋላ በቀጥታ ወደ ዝውውሩ በመግባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው እና ነባር የሆኑ ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችን ኮንትራት በማደስ ክረምቱን የጀመረው መቻል በመጨረሻም በይፋ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን በመንበሩ መሾሙ ይታወሳል። በተጫዋችነት ያሳለፉበትን ክለብ በአሰልጣኝነት ለማገልገል የአንድ ዓመት ውል የፈረሙት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝም የቀድሞ አጋራቸውን አሰልጣኝ ታደሰ ጥላሁን በትናንትናው ዕለት ምክትል አድርገው ወደ ስብስባቸው ማምጣታቸውን ዘግበናል።

አህመድ ረሺድ ፣ ቶማስ ስምረቱ ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ከነዓን ማርክነህ ፣ ምንይሉ ወንድሙ ፣ ዳግም ተፈራ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ በረከት ደስታ ፣ ውብሸት ጭላሎ እና ግርማ ዲሳሳን የ2015 የቡድኑ አካል ያደረገው ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቼ እና የት እንደሚያደርግ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡

በዚህም ክለቡ የፊታችን ሰኞ ነሀሴ 9 ረፋድ አዲስ አበባ ላይ የህክምና ምርመራ ለቡድኑ አባላት አከናውኖ ከሰዓት ወደ ቢሾፍቱ ከተማ በማምራት በአየር ሀይል ሜዳ ከማክሰኞ ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን  መከወን ይጀምራል፡፡