የሴካፋ የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር የጨዋታ ሰዓቶች ለውጥ ተደርጎባቸዋል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሳተፍበት የሴካፋ ዞን የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር የጨዋታ ሰዓቶች ማስተካከያ እንደተደረገባቸው ሶከር ኢትዮጵያ ከስፋራው መረጃ አግኝታለች።

በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የየሀገራቱ የሊግ አሸናፊ ክለቦች ከነገ ጀምሮ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም የማጣሪያ ፍልሚያቸውን ማድረግ ይጀምራሉ። የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ለዚሁ ውድድር ከትናንት በስትያ ወደ ስፍራው ያቀና ሲሆን የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውንም ከነገ በስትያ 7 ሰዓት ከዋሪየርስ ኩዊን ጋር እንዲያደርግ መርሐ-ግብር ተይዞለት ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ከስፍራው ባገኘችው መረጃ መሰረት ግን የውድድሩ አጠቃላይ የጨዋታ ሰዓቶች ለውጥ ተደርጎባቸዋል።

ውድድሩን በበላይነት የሚመራው ሴካፋ ረፋድ ላይ ተሳታፊ ክለቦችን በቲፋኒ ዳይመንድ ሆቴል ጠርቶ ባከናወነው ቴክኒካል ስብሰባ ላይም የደንብ ገለፃ ያደረገ ሲሆን ክለቦች በውድድሩ ላይ የሚጠቀሟቸውን መለያዎችንም እንዲያስተዋውቁ አድርጓል። በተጨማሪም የዐየር ፀባዩን ታሳቢ በማድረግ ሁሉም ጨዋታዎች የሰዓት ሽግሽግ እንደተደረገባቸው ይፋ አድርጓል።

በዚህም ከነ ጀምሮ የሚደረጉት መርሐ-ግብሮች የሦስት ሰዓት ሽግሽግ ተደርጎባቸው 10 እና 1 ሰዓት እንደሚደረጉ ተጠቅሷል። ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዋሪየርስ ኩዊን ጋር ሰኞ 7 ሰዓት የሚያደርገው የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ 10 ሰዓት በአዛም ኮምፕሌክስ የሚደረግ ይሆናል።