የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አምበል ሎዛ አበራ በቀጠናውን የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጋለች።
የወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የዞኑ የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር ለመሳተፍ ወደ ስፍራው እንዳቀና ይታወቃል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሊጉ ለቡድኗ 34 ግቦችን ያስቆጠረችው አጥቂዋ ሎዛ አበራም ስለቀጠናው የማጣሪያ ውድድር፣ የዝግጅት ጊዜ እና ግቧ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች።
ዝግጅት እንዴት ነው?
“ጥሩ የዝግጅት ጊዜ እያሳለፍን ነው። ፕሪምየር ሊጉ ካለቀ በኋላ ወዲያው ወደ ዝግጅት በመግባት ልምምዳችንን የጀመርነው። የመጡ አዲስ ተጫዋቾች አሉ ፤ ከእነሱ ጋር አንድ ላይ በመሆን እየሰራን ነው።”
ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ውድድሩ ማቅናታችሁ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ አለ?
“አምና ከዝግጅት ነው የሄድነው ፤ ሊጉ ከተቋረጠ ከረጅም ጊዜ በኋላ ማለት ነው። ሲቋረጥ ሲቀጥል ፤ ሲቋረጥ ሲቀጥል ነበር። አሁን ግን ውድድሩ ወዲያው ነው የታወቀው። ከውድድር በኋላ መሰባሰባችን ለእኛ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ዝግጅት ስታደርግ የጨዋታ ዝግጁነት (Match Fitness) ለማምጣት የሚከብድ ይመስለኛል። አሁን ግን ሁሉም ተጫዋች ለጨዋታ ዝግጁ የሆነበት እና በአዕምሮም የአሸናፊ መንፈስ ውስጥ ስላለ ያ ነገር እዛም ይቀጥላል ፤ እና ጥሩ ይመስለኛል።”
በአሸናፊነት ያጠናቀቃችሁት የሊጉ ውድድር እንዴት ነበር?
“በእርግጥ እየተቋረጠ እና እየጀመረ ነበር ውድድሩ የተካሄደው። በ20 ዓመት በታች ውድድር ምክንያት ረጅም ጊዜ ዕረፍት ላይ ነበርን። ከቀጠለ በኋላም ብዙ ፈታኝ ነገሮች ነበሩ። በክረምት ፣ በዝናብ እንድንጫወት እንዲሁም በየሁለት ቀን ልዩነት እንድንጫወት መሆኑ እጅግ በጣም ከባድ ነበር። ሁሉም ቡድኖች አንድ ቦታ ላይ ተሰብስበን ስለነበር የምንጫወተው አብዛኞቹ ቡድኖች ጥሩ ሁኔታ ላይ ነበሩ። በዛ ላይ ሁሉም ከእኛ ጋር ሲጫወቱ እንደ ዋንጫ ጨዋታ ነው የሚጫወቱት። ያ ነገር ውድድሩን ለእኛ ከባድ አድርጎብን ነበር። በመሀል ደግሞ የተወሰንን ተጫዋቾች ወደ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ሄደን ነበር። እዛ በነበርንበት ጊዜም ሙሉ አገልግሎት ነው የሰጠነው። እነዚህ እነዚህ ፈተናዎች ነበሩ። ሆኖም ግን ቡድኑ በአንድ አቋም በአሸናፊነት መንፈስ ተጋግዞ ሲሰራ ስለነበር ቻምፒዮን መሆን ችለናል።”
አምና የቻምፒዮንነት ውጥናችሁን አላሳካችሁም። ምክንያቱ ምን ነበር? ከዛስ ነገር ትምህርት ወስዳችኋል?
“አምናም እንደ አንድ ሆነን በጥሩ አሸናፊነት መንፈስ ነው የቀጠልነው። ሆኖም እግርኳስ ላይ መሸነፍ ፣ ማሸነፍ ፣ ከውድድር መውጣት የሚጠበቁ ነገሮች ናቸው። ባለን ሀሳብ እና የአዕምሮ ደረጃ የሚሰጡንን ልምምዶች በደንብ ሰርተን ለዋንጫ ተፋላሚ ሆነናል። በመጀመሪያ የውድድር ዓመት የተለያዩ ትልልቅ ቡድኖችን መግጠም ወይም ከምድባችን አልፈን በጥሎ ማለፉ ቀላል ውድድር አልነበረም ያደረግነው። ያንን አልፈን በመጀመሪያ ዓመት ልምድ እንዲህ ዓይነት ውጤት ማምጣት ቀላል አይደለም። ሁሌም ደግሞ እግርኳስ ራሱ በራሱ ስለሚያስተምርህ ከዛ በመነሳት ጥሩ ነገሮች ይመጣሉ ብዬ ነው የማስበው። ዘንድሮም ለቻምፒዮንነት ነው የምንሄደው። ስም ስለሚሰጠን ሳይሆን በተግባር ማሳየት ነው የምንፈልገው። የኢትዮጵያ ቡድን አምና ለዋንጫ ደርሷል ፤ ከፍ ያለ ግምት ሰጥተው እንደሚጠብቁን እርግጠኛ ነኝ። በብሔራዊ ቡድንም ስለሚያውቁን በብዙ እንደሚጠብቁን አስባለሁ። ነገር ግን እነሱ ከሚያስቡት ይልቅ እኛ በተግባር አሳይተን ቻምፒዮን ሆነን እንመጣለን ብዬ ነው የማስበው። ያንን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ተጫዋች ቁርጠኛ እንደሚሆን ነው የማስበው።”
አዳዲሶቹን የቡድኑን ፈራሚዎች እንዴት አገኘሻቸው?
“እኔ ስለመጡት ተጫዋቾች እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። በነበሩባቸው ክለቦች ጥሩ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከአዲሶቹ ፈራሚዎች ጋር አብሮ የመጫወት ዕድል ገጥሞኛል። በጣም ጠንካሮች እና ጎበዞች በዛ ላይ ወጣቶች ፣ ብዙ ማገልገል የሚችሉ ተስፋ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው። የእነሱ መምጣት ቡድናችንን ከፍ አድርጎታል። ምክንያቱም አዲስ ኃይል እና አቅም ይዘው ነው የመጡት። በልምምድ ቦታ ላይም አለመዋሀድ አይታይባቸውም። ቶሎ ተግባብተው ከእኛ ጋር ተዋህደው ጥሩ ሥራ እየሰሩ ነው። በመምጣታቸው እኛ በጣም ደስተኞች ነን። አንድ ላይ ተባብረን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለማስጠራት እና ሀገራችንንም ከፍ ለማድረግ ነው የምናስበው።”
እንደቡድንም ሆነ በግል በውድድሩ ላይ ምን አይነት ስኬት ማምጣትን ታልሚያለሽ?
“ጥሩ የውድድር ዓመት አሳልፈናል። እዛም ስንሄድ እዚህ ከነበረውም በላይ ከባድ ፈተና ይጠብቀናል። ብዙ ጊዜ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች እጅግ ፈታኝ እና ሁል ጊዜም በተሻለ አቅም እና ጉልበት እንድትገኝ ነው የሚያደርጉት። ይህንን ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት እያወራን እንዲሁም አሰልጣኞቻችንም እየነገሩን ነው ያሉት። ያንን እሳክተን እንደቡድን ቻምፒዮን ሆነን ለመምጣት ነው የምናስበው። እኔ በግሌ ደግሞ ሁሌም ቢሆን ፉክክሬ ከራሴ ጋር ነው። በራሴ ማድረግ እንዳለብኝ አምናለሁ። ሁሌ አሸናፊ እንደሆንኩ እና ማድረግ እንደምችል ፣ ትልቅ ተጫዋችም እንደሆንኩ ከራሴ ጋር ነው ፉክክሬ። በዛ ውድድር ላይም አምና ኮከብ ግብ አግቢ ነበሩኩ። ያንን ለማስጠበቅ እና በውድድሩ ላይም የተሻለች ተጫዋች ሆኜ ለመመምጣት ነው የማስበው።”