ቡናማዎቹ የአሰልጣኝ ቡድናቸውን አደራጅተው መጨረሳቸውን ይፋ አድርገዋል።
ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር በመለያየት አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን የሾመው ኢትዮጵያ ቡና ራሱን በዝውውሮች ሲያጠናክር ቆይቶ የከርሞው ቡድኑን በመያዝ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት አምርቷል። ዛሬ ክለቡ በማህበራዊ ሚዲያው ይፋ ባደረገው መሰረት ደግሞ ከዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ አራት ባለሙያዎችን በአሰልጣኝ ቡድኑ ውስጥ ማካተቱ ታውቋል።
በምክትል አሰልጣኝነት ቦታ ላይ የቀድሞው የክለቡ ተጫዋች እና የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች አሰልጣኝ የነበረው ዮሴፍ ተስፋዬ እንዲሁም ከዚህ ቀድም ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በወልቂጤ ከተማ ውስጥ አብሮ የሰራው ነፃነት ክብሬን መሾማቸውን ክለቡ አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ ከድረ ገፃችን ጋር ቆይታ ያደረገው እና በሀገረ እንግሊዝ በእግርኳሳዊ ትምህርቶች እንዲሁም በስራ ላይ ያሳለፈው ሚካኤል ኃይሉ የቡድኑ የስነ አዕምሮ እና የአካል ብቃት አሰልጣኝ ሆኖ ሲቀላቀል የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ኮከብ ታፈሰ ተስፋዬ ደግሞ በምክትል ቡድን መሪነት ቦታ ላይ መሾሙ ታውቋል።