አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከነገው ጨዋታ በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል

👉”ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አደገ ማለት የኢትዮጵያ እግርኳስም አደገ ማለት ነው”

👉”ፕሮጀክት አይደለም እየሰራሁ ያለሁት ፤ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ላይ ነው እየሰራው ያለሁት…”

👉”ያሳረፉን ገበያ መሐል ነው ፤ ቦታውም ትንሽ ደስ አይልም”

👉”ዓምና ግብፅን በቀዳዳ አይተን ነው የተመለስነው አሁን ግን ሞሮኮን በሙሉ ዐይናችን ለማየት የሚያስችለንን ትኬት ለመቁረጥ ነው ታንዛኒያ የደረስነው”

👉”እንደሚታወቀው አሠልጣኝ እና ነጋዴ አያኮርፍም”

የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባለቤቱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለተኛ ጊዜ በሚከናወነው ትልቁ የእንስት የክለቦች ውድድር ላይ ለመሳተፍ የዞኑን የማጣሪያ ፍልሚያ ለማከናወን ከሦስት ቀናት በፊት ወደ ታንዛኒያ እንዳመራ ይታወቃል። የቀጠናው ውድድር ዛሬ የተጀመረ ሲሆን የሀገራችን ተወካይ የሆነው እና በምድብ አንድ ከዛንዚባሩ ዋሪየርስ ኩዊን፣ ከቡሩንዲው ፎፊላ እና ከሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ ጋር የተደለደለው ባንክም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ነገ 9 ሰዓት በአዛም ኮምፕሌክስ ያከናውናል። ሶከር ኢትዮጵያም ያለፉትን ተከታታይ ቀናት ክለቡን እና ውድድሩን የተመለከቱ መረጃዎችን ወደ እናንተ ስታደርስ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከነገው ጨዋታ በፊት የቡድኑን ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አግኝታ ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ለወሳኙ ውድድር እያደረጋችሁ ያላችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል?

“ዝግጅት ጥሩ ነው። በመልካም ሁኔታ እየተዘጋጀን ነው። በቅድሚያ 25 ተጫዋቾችን ይዘን ነበር ፤ ከዛ ደግሞ 20 ተጫዋቾችን አጣርተን ወደ ታንዛኒያ አምርተናል።”

የዓምናው ውድድር እንዴት ነበር? ከዓምናው ውድድር የወሰዳችሁት ትምህርት ምንድን ነው?

“ዓምና ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደረግ እኛም የመጀመሪያ ተሳትፏችንን አድርገን ነበር። እንደ መጀመሪያው ውድድር ጥሩ ነበር። በታሪክ በወንዶች ደረጃ ያን ያህል ርቀት የተጓዘ ክለብ ያለን አይመስለኝም ፤ በሴቶች ግን እኛ ጥሩ ነገር ለማምጣት ጥረናል። እርግጥ በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ጥሩ ስኬቶች መተዋል። የእኛ ውጤት እንደ ሀገር ትልቅ መነቃቃት አምጥቶ ከ20 ዓመት በታች እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም ከ17 ዓመት በታች ቡድኖች ላይ የመጣው ውጤት ይታወቃል። ስለዚህ እኛ ጫፍ መድረስ እንደሚቻል አሳይተንበት ከኋላችን የመጡት ደግሞ መጨረስ እንደሚችሉ ያየንበት ነው።

“በስብስባችን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ዓምና ውድድሩ ላይ የተሳተፉ እና ውድድሩን የሚያውቁ ናቸው። ይሄ ትልቅ እድል ነው። ስለዚህ ተጫዋቾቹ የውድድሩን መንፈስ እና ባህሪ ያውቁታል። ዓምና ያለማወቅ ችግሮች ነበሩብን። አሁን ግን እንደዚህ የሚባል ነገር የለም። ይህ ቢሆንም ግን ጥሩ ውድድር ነበር አድርገን የተመለስነው። ከምንም በላይ ዓምና ኬኒያ ላይ በጣም ተከብረናል። እዚህ (ኢትዮጵያ) ሁሌ ስታሸንፍ ደስ የማይላቸው ይኖራሉ። እዛ ቋንቋውንም ስለማናውቅ ይስደቡብም ይርገሙንም አናውቅም። ሜዳ ላይ ብቻ በእግር ኳስ ነበር የምንገናኘው። አሁን ደግሞ ከውድድር ወዲያው ወደዚህ ፍልሚያ አቅንተናል። ከውድድር መምጣታችንን እንደ ጥሩ ነገር ነው የምንጠቀመው። ዓምና ረዘም ያሉ ወራት ርቀን ነበር ውድድሩን ያደረግነው። በተጨማሪም ውድድሩ ይጀመራል ከተባለበት ጊዜ ሲራዘም ሲራዘም ቆይቶ ነበር። ይሄ ትንሽ ረብሾን ነበር። አሁን ግን ይሄ አልሆነም። አንዴ ብቻ ነው የተራዘመው። የሆነው ሆኖ በጥሩ ዝግጅት ላይ ነን ፤ ያለንበት የሥነ-ልቦና ደረጃም ጥሩ ነው።”

በዚህ ውድድር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የምትሳተፉት ፤ ከዓምና ዘንድሮ ቡድናችሁ ላይ ምን እድገት ጨምራችሁ ነው ውድድሩን የቀረባችሁት? ስብስባችሁንስ እንዴት አዋቅራችሁ ነው ወደ ታንዛኒያ ያቀናችሁት?

“አንድ ነገር መግለፅ እፈልጋለው። ዓለም ላይ የሚደረግ ግን እኛ ስናደርገው ጉርምርምታ የሚያመጣ ነገር አለ። አላቅም ለምን እንደሆነ ግን አሠልጣኞች ክለባቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደረጃ የጠየቁትን ስለማይመልስላቸው ሰበባሰበብ የሚያበዙ ሰዎች የሚፈጥሩት ነገር ነው። እኛ ምንም ማድረግ አንችልም። ስራችንን ነው የምንሰራው። እኛ ራሳችንን እያጠናከርን ነው። ነገም ጥሩ ተጫዋቾችን ካገኘን እናስፈርማለን። ምክንያቱም ፕሮጀክት አይደለም እየሰራሁ ያለሁት ፤ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ላይ ነው እየሰራው ያለሁት። ስለዚህ ጎበዝ ታዳጊዎውንን ሆነ ወጣቶችን እንወስዳለን። በዚህ አጋጣሚ አዳማ ናርዶስን፣ ድሬዳዋ ብርቄን፣ አዲስ አበባም አርየትን እንዲሁም መከላከያ መሳይን በዚህ ትልቅ ውድድር ላይ እንድንጠቀም ተጫዋቾቹን ቶሎ ስለለቀቁልን በጣም እናመሰግናለን። አንድ ተጫዋች (ቅድስት ዘለቀ) በቤተሰብ ችግር አልተቀላቀለችንም። ከእነሱ ውጪ እኛ ጋር የነበረችው ንቦኝ የን ኢትዮ አሌክትሪክ ከመግባቷ በፊት በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ብቃት አሳይታ ነበር። እኛም በዛ ብሔራዊ ቡድን ባሳየችው ብቃት ተቆጭተን ለማምጣት ወስነን ነበር። እንደሚታወቀው አሠልጣኝ እና ነጋዴ አያኮርፍም። አሠልጣኝ ፍሬው ደፍሮ ተጫዋቿን እንደዚህ ማምጣቱ ሊመሰገን ይገባል። እቺንም ተጫዋች ለማስፈረም ጥረን ውድድር ባይኖርም ከኤሌክትሪክ ጋር የ26 ቀን ውል ስላላት ክለቡ ፍቃደኛ ባለመሆኑ መፈረም አልቻለችም። እኛ የክለቡን ሀሳብ እናከብራለን። ግን በእግርኳሳችን ትብብር የሚባለው ነገር በደንብ ቢለመድ ጥሩ ነው። እኔ ከሁሉም አሠልጣኞች ጋር ምንም ችግር የለብኝም። ከሁሉም ጋር ጥሩ አክብሮት አለኝ። አንዳንድ አሠልጣኞች ግን ደሞዝ እንዲጨመርላቸው ወይም ተቀባይነት እንዲያገኙ የእኔን ስም ያነሳሉ። ዞሮ ዞሮ መተባበር በአምሯችን ሊኖር ይገባል። ዓምና ቪሂጋ ኩዊንስ ዋንጫ ሲያነሳ መጀመሪያ ስናሸንፈው እንዴት ሊያሸንፈን ቻለ ብለው አሠልጣኞቹ ተሰባስበው የእኛን ቡድን ሲያጠኑ ነበር። እንደዚህ አይነት ነገሮች ሀገራችን ላይም መዘውተር አለባቸው። አለመተባበራችን ብዙ ነገር ያጎልብናል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አደገ ማለት የኢትዮጵያ እግርኳስም አደገ ማለት ነው።”

ታንዛኒያን እንዴት አገኛችሁት?

“እውነት ለመናገር አቀባበሉ ትንሽ ደስ አይልም። እኛ የጠበቅነው እንደ ኬንያ ነበር። ያሳረፉን ገበያ መሐል ነው። ቦታውም ትንሽ ደስ አይልም። ትኩረት ለማድረግ ትንሽ የማይመመች ሆቴል ነው። ግን ተጫዋቾቹ ይሄንን የአፍሪካ ችግር ስለሚያውቁ በደንብ ተረድተውታል። እኛ እና የጅቡቲው ክለብ አንድ ላይ ነው ያረፍነው። የጅቡቲውን ክለብ እንደውም ከእኛ የከፋ መብራት የሌለበት ቦታ ነበር ያሳረፉዋቸው። ምንም ማድረግ አይቻልም። ዓምና ኬኒያዎች ሪዞርት ነበር ያሳረፉን። እንደዛ ይሆናል ብለን ጠብቀን ነበር ግን አልሆነም። ግን እኛ ከጃን ሜዳ ነው የወጣነው። እዛ በርካታ ችግሮችን አልፈናል። አሁን ያሉትን ችግሮች ተጫዋቾቹ ከእኔ የበለጠ ተረድተውታል። ኬኒያ ላይ እንደነበረው አደለም አሁን የገጠመን። ግን ይሄ ችግር እንደውም በደንብ አድርጎ ያበረታናል።”

በውድድሩ ያላችሁ እቅድ ምንድን ነው?

“እቅዳችን ከዓምና የተሻለ ነገር ማስመዝገብ ነው። ይህ ማለት ዓምና 2ኛ ነበር የወጣነው ስለዚህ አሁን አንደኛ ማለት ነው። ይሄ ነው ዋነኛ እቅዳችን። ግን ይሄ እግርኳስ ነው። የሚፈጠረው ነገር አይታወቅም። የሚፈጠረውን ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነን። ግን ተጫዋቾቼ በቂ ብቃት ስላላቸው በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጁ ነው። ሻምፒዮን የመሆን በቂ አቅም እንዳለንም ይሰማኛል። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ጨዋታዎች በትኩረት እናደርጋለን። በአጠቃላይ ዓምና ግብፅን በቀዳዳ አይተን ነው የተመለስነው አሁን ግን ሞሮኮን በሙሉ ዐይናችን ለማየት የሚያስችለንን ትኬት ለመቁረጥ ነው ታንዛኒያ የደረስነው።”

ያጋሩ