የምርጫ አስፈፃሚ እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መግለጫ ሰጥተዋል

12 ቀናት የቀሩት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና ሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫን የተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል።

ዛሬ ከሰዓት በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት የተሰጠው መግለጫ ነሐሴ 22 በጎንደር ከተማ የሚደረገውን ምርጫ የተመለከተ ነበር። በመግለጫው ላይ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሦስት አባላት እንዲሁም የምርጫው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሁለት አባላት ተገኝተው በእስካሁኑ የሥራ ሂደታቸው ላይ የመጡበትን መንገድ ያብራሩ ሲሆን ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል።

የዕለቱን ቀዳሚ መግለጫ የሰጡት የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኃይሉ ሞላ ነበሩ። ሰብሳቢው እስካሁን ኮሚቴው ያከናወነውን ሥራ ሲያስረዱ ከሐምሌ 5-19 የዕጩዎች ማመልከቻ በመቀበል እስከ ሐምሌ 26 ድረስ ደግሞ የዕጩዎችን ተገቢነት በመመርመር 3 ለፕሬዘዳንትነት 26 ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት የሚበቁ ተመራጮችን በማሳወቅ እንደቆየ ተናግረው በቀጣይ
የዕጩዎችን ፕሮፋይል ማዘጋጀት ፣ የምርጫ ወረቀቶች እና የምርጫ ሳጥን ማዘጋጀት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በመከወን የምርጫውን ዕለት እየተጠባበቀ ስለመሆኑ ተናግረዋል። “የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውን ውሳኔዎች በመመርኮዝ በቀጣይ ሁለት ቀናት ውስጥ የዕጩዎችን ዝርዝር እናሳውቃለን።” ሲሉም መድረኩን ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ብርሀኑ ከበደ አስረክበዋል። አቶ ብርሀኑ በመካከላቸው የነበሩት የሕግ ሰው ሁለት ጊዜ ሲሰበስቡ ባለመገኘታቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባሉት አባላት ለመወጣት ሲሰሩ መቆየተቸውን በመግለፅ መድረኩን ለጥያቄ እና መልስ ክፍት አድርገዋል።

በጥያቄ እና መልሱ ወቅት የነበሩ አንኳር ሀሳቦች የሚከተሉት ነበሩ።

ፊፋ እና ካፍ በኮሚቴው አባላት ላይ የተገቢነት ጥያቄ አንስተዋል ሰለመባሉ …

አቶ ኃይሉ “እስካሁን ሰዓት ድረስ ስም ዝርዝራችን ለካፍም ለፊፋም ተልኳል። እስካሁን ፊፋም ሆነ ካፍ ያደረሰን ምንም ጥያቄ የለም። ጠቅላላ ጉባኤው መርጦናል ፤ ላለፉት 54 ቀናት ሥራችንን እየሰራን ነው ያለነው። በተሰጠን ኃላፊነት ሕጉን መሰረት አድርገን እየሰራን ነው ያለነው። ለፊፋ ቀርቧል መባሉን እኔም እንደናንተ በውጪ እሰማለሁ። ሆኖም ለኮሚቴው የደረሰ ምንም ነገር የለም ፤ እስካሀኑ ሰዓት ድረስ።”

ምርጫው በታቀደለት ቀን ስለመከናወኑ…

አቶ ኃይሉ “በትክክል ! በደንብ አድርጎ ይፈፀማል። ምክንያቱ ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ያሳለፈበት ጉዳይ በመሆኑ ነው። ኮሚቴውን ያዋቀረው ጠቅላላ ጉባዔው ነው። በዕለቱ ሪፖርት ሲቀርብለት ጉባዔው የሚያነሳው ነገር ካለ እዛው የምናየው ይሆናል። እስካሁን ባለኝ መረጃ ግን ምንም ዓይነት የተነሳ ጥያቄ ባለመኖሩ ምርጫው በተያዘለት ዕለት ይከወናል።”

ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻር ካምፓኒ በሰጠው መግለጫ መነሻነት ‘የኮሚቴ አባላቱ የፌዴሬሽኑ አካላት እና አባላት በመሆናቸው የተገቢነት እና የጥቅም ግጭት ጉዳይ ይነሳባቸውል’ የሚለው ነጥብ ሰፊ ጊዜ የወሰደ የመግለጫው ክፍል ነበር።

ይህንን አስመልክቶ “ሻር ካምፓኒው የጠቅላላ ጉባኤ አባል አይደለም። እንደ አንድ ይመለከተኛል እንደሚል አካል አስተያየት መስጠት ግን ይችላል።” ያሉት አቶ ኃይሉ የፌዴሬሽኑ አካላት የሚባሉት እና በምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የማይካተቱት የፌዴሬሽኑ የፍትህ ኮሚቴዎችን የሚመለከት መሆኑን በሰፊው አስረድተው የፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ መንግሥቱ ማሩ ይህንን ኃላፊነታቸውን በመተው አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ መግባታቸውን እንዲሁም ራሳቸው አቶ ኃይሉም ፌዴሬሽኑን በጠበቃነት ያገለገሉት ከአምስት ወራት በፊት መሆኑን አንስተው የተገቢነት ጥያቄ እንደማይነሳባቸው ተናግረዋል። ከፌዴሬሽኑ ‘አካላት’ በተጨማሪ ‘አባላት’ ተብለው የተገለፀውን በተመለከተም አቶ ኃይሉ ሲያብራሩ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት የሚባሉት የክልል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች እና ክለቦች መሆናቸውን በማስታወስ በእነዚህ ተቋም ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በምርጫ አስፈፃሚነት ለመሳተፍ ሕጉ እንደማይከለክላቸው በሰፊው ገልፀዋል።

ከዚህ ቀድም በነበረው የምርጫ ኮሚቴ እንደገና መዋቀሩ ዘንድሮም ሊከሰት ስለመቻሉ…

አቶ ኃይሉ “ያ እኔ ይሄ ሙሉ ለሙሉ ይለያያል። ያኔ ከጠቅላላ ጉባዔ ተመረጡ ፤ ምርጫ ኮሜቴውም ይግባኝ ሰሚውም ሁለት ቦታ ተሰነጠቀ። ሊስማሙ አልቻሉም። ፊፋ መጥቶ ሌላ አስመራጭ ኮሚቴ በመምረጥ ስራው ቀጠለ። ይህችን ነገር እኛ ጋር ለማምጣት ብዙ ተሞክሯል። እኛን ለመሰንጠቅ ተሞክሯል ፤ የለም አይሆንም። እኛ ሙያችንን እና ሥራችንን አክብረን የምንሰራ ሰዎች ነን።” በማለት በዚህ መነሻነት ከፊፋ የሚመጣ ቅጣት እንደማይኖር ጠቁመዋል።

አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ስላነሱት ቅሬታ..

አቶ ኃይሉ “በዕጩ ዝርዝራችን ውስጥ አቶ ገዛኸኝ የሉም። አቶ ገዛኸኝ ለእኛ ዕጩ አይደሉም። ዕጩዎችን በተመለከተ ባለቤቶቹ ክልሎች ወይም ከተማ አስተዳድሮች ናቸው። ከተማ አስተዳደሩ ይሄንን ሰው አልደገፈውም። ስለዚህ የእኛ እጩ አይደለም። ”

ሌላኛው የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መንግሥቱ ማሩም የኮሚቴውን ሥራ በመጨረሻ እውቅና የሚሰጠው ጠቅላላ ጉባኤው ብቻ መሆኑን አዕንኦት ሰጥተው ካስረዱ በኋላ እሳቸውን ስለተመለከተው የተገቢነት ጥያቄ ይህንን ብለዋል…

“የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባል ነበርኩ። ግንቦት 7 ላይ የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ሲደረግ እና ስመረጥ አልተገኘሁም ነበር። ከተመረጥን በኋላ የመጀመሪያ ስብሰባ ስናደርግ ግን ይሄንን ጥያቄ አንስቼ ነበር። ሁለት ቦታ መሆን እንደሌለብኝ አንስቻለሁ። በእርግጥ ይግባኝ ሰሚ እና ዲስፕሊን ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለፅህፈት ቤቱ ሳይሆን በራሱ ገለልተኛ አካል ነው። ቢሆንም እዛ ውስጥ መግባት እንደሌለብኝ አንስቻለሁ። ሆኖም በደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መነሳቴ ተነግሮኛል። እዚህ ለመግባት አይደለም የወጣሁት ወይም ይሄን ስጨርስ የምመለስበት አይሆንም። ሌላው እኔ የምሰራው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ውስጥ ነው። የድርጅቱ ከፍተኛ አስተዳደር ውስጥ አለሁ። ስፖርት ፅህፈት ቤቱ ደግሞ የራሱ ኮሚቴ እና ፅህፈት ቤት አለው ፤ እዛ ውስጥ የለሁም። ተቋሙ የፋይናንስ ተቋም ነው። በተቋሙ የፋይናንስ አስተዳደር ውስጥ በመሆንህ እዚህ ኮሚቴ ውስጥ መግባት የለብህም የሚል ካለ እኔ ምንም ችግር የለብኝም ይሄንን መውሰድ ይቻላል።”

ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ ደግሞ በሕጉ መሰረት በኮሚቴው ውስጥ የሕግ ባለሙያ አለመኖሩ ስራቸው ላይ ስላለው ተፅዕኖ አቶ ብርሀኑ ከበደ ሲናገሩ

“እያንዳንዱን ውሳኔ በራሱ መንገድ በሕጉ ላይ ተመስርተን ማየትን ነው የመረጥነው። በዛ መንገድ ነው የሄድነው” በማለት “እኛንም ልቀቁን ወደ ማለቱ ደርሰን ነበር። ግን ጠቅላላ ጉባዔው አምኖብን ኃላፊነት በመስጠቱ ለመውጣት መሞከር ነበረብን።” ብለዋል።

የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የአቶ ገዛኸኝ ወልዴን አቤቱታን ስላለመመልከቱ ደግሞ በሰጡት ሀሳብ

“በጉዳዩ ዙሪያ ዋና ሰብሳቢውንም አስጠርተን አናግረናል ፤ ዝም ብለንም አልወሰንም። የራሳችንን ሀሳብ ሳንናገር የእሳቸውን ምልከታ አድምጠናል። መነሻችን ያ ነበር። ሕጉ በሚፈቅድልን መሰረት የሌሎቹን ለየብቻ አይተናል። እሳቸው (አቶ ገዛኸኝ) ግን በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ በሌሉበት ሁኔታ መናገር አንችልም። በማስፈፀሚያ ደንቡ ላይም እኛ ምርጫ አስፈፃሚው ያየውን ጉዳይ ነው እንጂ የምናየው የመጣልንን ሁሉ አናይም።” ብለዋል።

ከዚህ በኋላም መግለጫው ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ከተነሱበት እና ከመድረኩ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ያጋሩ