“ክለባችን ኩራታችን ” በሚል ስያሜ በሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ አማካኝነት በሚደረገው የሩጫ መርሐግብር ዙሪያ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከጅምሩ አንስቶ በመሳተፍ ላይ እስከ አሁን የዘለቀው ሀዋሳ ከተማ እግርኳስ ክለብ ከደጋፊ ማህበሩ ጋር በጣምራ በመሆን በያዝነው ነሐሴ 29 ላይ በሚያዘጋጀው ሩጫ መርሐግብር ዙሪያ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል አመሻሹን መግለጫ ተሰጥቷል።
የክለቡን አቅም ማሳደግ እና ደጋፊዎችን በደንብ ክለቡን መደገፍ ይችሉ ዘንድ ዓላማን አድርጎ በተዘጋጀው በዚህ መግለጫ ላይ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ደርጊቱ ጫሌ ፣ የከተማው ስፖርት ኮሚሽነር እና የክለቡ የቦርድ አባል አቶ ጥላሁን ሀሜሶ ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሁቴሳ ሁጋሞ ፣ የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ባዩ በልጉዳ እና አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በተገኙበት መግለጫው ለጋዜጠኞች ተሰጥቷል፡፡
የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ደርጊቱ ጫሌ በመነሻ በንግግራቸው ተከታዩን ሀሳብ አንስተዋል፡፡ “ይህ ትልቅ ክለብ ነው ፤ ክለቡን ወደ ታላቅነት ለመመለስ በርካታ ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን። ይህ ሩጫም በክለቡ እና በደጋፊ ማህበሩ አማካኝነት መዘጋጀቱ ከሥራዎቹ መሀል አንዱ ነው፡፡ በዚህ ውድድር የክለቡ ደጋፊዎች በአጠቃላይ ይሳተፋሉ ብለን እናስባለን፡፡ በህፃናት እና በአዋቂዎች ከ15 እስከ 20 ሺህ ተሳታፊ ይኖራል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሁሉም በዚህ ውድድር ተሳታፊ መሆን እንዲችል ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ”፡፡ ሲሉ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል፡፡ በመቀጠል የክለቡ የቦርድ አባል አቶ ጥላሁን ሀሜሶ “ክለባችን ኩራታችን መሆኑን ለሁሉም ማሳየት አለብን ይህንን በተግባር ለማሳየት ሁሉም በንቃት በዚህ ውድድር ላይ ሊሳተፍ ይገባዋል፡፡ በዚህ ሩጫ ላይ ክለቡን ከመደገፍ ባለፈ የክለቡን ታሪክ እና የከተማዋን ገፅታ በደንብ ለሌላው ማህበረሰብ ለማስተዋወቅም ትልቅ ድርሻ ይኖረዋልም”፡፡ ብለዋል፡፡
የክለቡ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ባዩ ባልጉዳ በበኩላቸው “ይህ ውድድር ሲዘጋጅ ከስድስት ዓመት በኋላ ነው፡፡ በቀጣይ ግን በየዓመቱ ይደረጋል፡፡ የክለቡን የቀደመ ገናናነት ለመመለስ ተያይዘን መስራት ይኖርብናል፡፡ ይህ አንጋፋ ክለብ ነው። የክለቡ መለያ ለብሶ መሮጥ ኩራት ነው፡፡ ሁሉም የክለቡ ደጋፊ ከጎናችን ሆኖ በዚህ መርሐግብር እንዲሳተፍ ጥሪን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ”፡፡ ሲሉም ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ውድድሩ 5 ኪሎ ሜትሮችን እንደሚሸፍን የተነገረ ሲሆን ከውድድሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በክለቡ ውስጥ በ1996 እና 1999 የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ እንዲሁም ደግሞ 1997 የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ሲሆን በክለቡ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የእግርኳስ ጨዋታን የሚያከናውኑ ሲሆን ለክለቡ ባለውለታዎችም ዕውቅና እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡