በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሀዲያ ሆሳዕና ያሳለፉት አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለዲሲፕሊን ኮሚቴ የክስ ደብዳቤ አስገብተዋል።
አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የዘንድሮ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት ከቤራዎቹን ለማሰልጠን የሁለት ዓመት ውል መፈረማቸው ይታወቃል። በ2014 የሊጉ ውድድርም 10ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው የሚታወቅ ሲሆን ውድድሩ ካለቀ በኋላ ግን አሠልጣኙ ተከስተዋል ያሏቸውን ችግሮች በመዘርዘር “በጋራ ውል ስምምነት ውላችንን እናቋርጥ” ብለው በ30/10/2014 ደብዳቤ ለክለቡ አስገብተው ነበር። እርግጥ አሠልጣኙ ከዚህ ደብዳቤ በፊት ክለቡ እንዲጠናከር በተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ተሳትፎ እንዲደረግ ያለበለዚያ ሀላፊነት እንደማይወስዱም ቀድመው ደብዳቤ ለክለቡ ማስገባታቸውን ዘግበን ነበር።
እንደገለፅነው አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ውላቸው “በጋራ ስምምነት እንዲቋረጥ” ጥያቄ ቢያቀርቡም ሁለቱ አካላት በጠረቤዛ ዙሪያ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ እንደቀሩ ተሰምቷል። አሠልጣኙም “ውሉ በጋራ ስምምነት መቋረጥ ስላልቻለ የሰኔ እና የሐምሌ ወር ደሞዜ ተከፍሎኝ የውል ግዴታዬን እንድወጣ ወደ ስራ ገበታዬ ልመለስ” በማለት ሌላ ደብዳቤ አስገብተው ካልሆነ ግን መብታቸውን በህግ አግባብ እንደሚጠይቁ ገልፀው ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ሀዲያ ሆሳዕና በ29/11/2014 በፃፈው የመልስ ደብዳቤ አሠልጣኙን በጠየቀው መሠረት ውሉ እንደተቋረጠ እና የ2015 የቅድመ ክፍያ ገንዘብ እንዲመልስ ለአሠልጣኙ መልስ ሰጥቶ ነበር።
አሁን ደግሞ ሶከር ኢትዮጵያ የአሠልጣኙን ጉዳይ ከያዙት የህግ አማካሪ እና ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ጉዳዩ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ አምርቷል። በዚህም አሠልጣኙ “ሀዲያ ሆሳዕና ከአመልካች ጋር የፊርማ ውል ማፍረስ ስምምነት ሳይፈፅም በራሱ ፍቃድ ውል ያፈረሰ መሆኑን የገለፀ ስለሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ከአሰልጣኙ ጋር ውል ያፈረሰው ህገ ወጥ ድርጊት በመሆኑ ሀዲያ ሆሳዕና በራሱ ፍቃድ ያፈረሰውን ውል በማፅደቅ ቀሪ የውል ወራት ዘመን ደሞዙን እስከ ሰኔ 30 2015 (15 ወራት) ድረስ እንዲከፍል” በማለት ጥያቄ አቅርቧል።