የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ ቦታ ተቀይሯል

ነሐሴ 21 እና 22 ቀን 2014 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሊካሄድ መርሐ ግብር ተይዞለት የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤን ቦታ እንዲቀየር ውሳኔ መተላለፉን ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።

ከፌዴሬሽኑ ድረ-ገፅ ያገኘነው መረጃ ይህንን ይመስላል:-

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጠቅላላ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ለመገምገም በዛሬው ዕለት ነሐሴ 12/12/2014 ዓ.ም ለማካሄድ ጥሪ አድርጎ የነበረ ቢሆንም አባላቱ ባለመሟላቱ ጉዳዩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኢመርጀንሲ ኮሚቴ እንዲመለከተው በተወሰነው መሠረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኢመርጀንሲ ኮሚቴ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

” የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነሐሴ 21 እና 22 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጎንደር ከተማ የሚካሄደው የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት በጎንደር ከተማ አስተዳደር በኩል ጥሩ መሆኑ የተገመገመ ቢሆንም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የጠቅላላ ጉባኤ ሥራ ወደሚያከናውኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን ሰራተኞች ስልክ በመደወል ከክልሉ ክለቦች የተላኩ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ወኪሎች ስሞች መቀየር እንዳለባቸው እና ይህንን እንዲያደርጉ ፤ ካላደረጉ ግን ጉባኤው እንዲስተጓጎል እንደሚያደርጉ በማስፈራራት ጭምር ስሜታቸውን መግለፃቸው ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል፡፡

” ይህ ታላቅ የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ ከጉባኤው አባላት በተጨማሪ የፊፋ እና የካፍ ታዛቢዎች የሚታደሙበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የክልሉ ከፍተኛ አመራር ሆነው ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ መሥራት ሲገባቸው ችግር እንደሚፈጥሩ መግለፃቸው የጉባኤው ውጤታማነት ላይ ስጋት እንዲያድርብን ምክንያት ሆኗል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር እያደረገ ያለው ተግባር ፍፁም የሚያስመሰግነው ቢሆንም ፤ የክልሉ አመራር በዚህ ደረጃ ችግር ለመፍጠር እየሞከሩ በመሆኑ እና ሌሎች የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ ያለን ጊዜ አጭር በመሆኑ የጉባኤውን ቦታ መቀየር አስፈላጊ መሆኑን ኢመርጀንሲ ኮሚቴው አምኖበታል። ስለዚህም ጉባኤው አዲስ አበባ ከተማ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በቀጣይ ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄድበትን አዳራሽ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በቀጣይ የምናሳውቅ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡ “