የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ለሊግ ካምፓኒው መግለጫ መልስ ሰጥተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ ላይ ፌዴሬሽኑን በኮነነባቸው ነጥቦች ዙሪያ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ምላሾችን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና ሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ሊከናወን ቀናቶች ቀርተውታል። ከምርጫው መደረግ አስቀድሞ በእግርኳሱ አመራሮች እና ተቋማት በኩል የሚሰጡ አስተያየቶችም ትኩረት እንደሳቡ ቀጥለዋል። ከእነዚህ መካከል ከዘጠኝ ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ አማካይነት ሰፋ ያለ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። “የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ውስጥ የሚኖር ሰላም ሆነ ውጥረት በአጠቃላይ የእግርኳሱ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል” የሚል መነሻ በነበረው በዛ መግለጫ ላይ ሊግ ካምፓኒው ከእግርኳስ ፌዴሬሽኑ በርካታ ችግሮች መካከል ማሳያ ይሆናሉ ያላቸውን ሦስት ነጥቦች በማንሳት ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር።

ይህንን ተከትሎ ዛሬ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት መግለጫ የጠሩት የተቋሙ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በሦስቱ ጉዳዮች እና በአጠቃላይ በሊግ ካምፓኒው መግለጫ መነሻ እና መድረሻ ላይ ያተኮረ የ28 ደቂቃ ገለፃ አድርገዋል።

የመጀመሪያው ጉዳይ የሆነው ፌዴሬሽኑ አሁን የሚገለገልበት እና በፊፋ ድጋፍ በ95 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዛው ሕንፃ ስም ዝውውር አለመፈፀሙ በሊግ ካምፓኒው የመነሳቱ ነገር ነበር። ፕሬዝደንቱ ሕንፃውን በመግዛት ሂደት ውስጥ ከፊፋ ጋር ስለነበራቸው ምልልስ እና የጨረታ ሂደት ካስረዱ በኋላ ጥያቄ በተነሳበት ስም ያለመዞሩ ጉዳይ ላይ “ሕንፃው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሕንፃ ነው። ኦሪጅናል ካርታ አለን ፣ ሙሉ ውክልና አለን ፤ ተቋሙ ይሄንን ሕንፃ መሸጥ እፈልጋለሁ ቢል ይችላል ፤ የሚከለክለው ሕግ የለም። ስሙን ለማዞር ብዙ ርቀት ሄደናል። በመጀመሪያ ባሉት ኤክስፐርቶች ምክንያት ዛሬ ነገ እያሉ ቆይቷል ፤ በዛን ሰዓት አሹራው 6 ሚሊየን ብር ነበር ፤ ያን ለመክፈል አቅም የለንም ነበር። ስለዚህ ዝም ነው ያልነው። በኋላ አቅም ስናደራጅ ለመክፈል ስንሄድ ተጨማሪ 8 ሚሊየን እንዳለ ነገሩን። 8 ሚሊየኑ የካፒታል ጌይን ነው። ‘ይሄንን አንከፍልም’ ብለን የመጀመሪያውን ወደ 5.8 ሚሊየን አካባቢ ከፍለናል። ያኛውን ወደ ህግ ወሰድን ፤ በህጉ መሰረት ጥቅም ያገኘው እና መክፈል የሚገባው ሕንፃውን ለእኛ የሸጠው ሰው ነው። ይህንን ተከትለን ስንሄድ ክፍያው የማይፈፀም ከሆነ ስሙ እንደማይዘዋወር ነው የነገሩን። በዚህም መሰረት ጉዳዩን ለህግ ባለሙያ ሰጥተናል።” በማለት እና ተያያዥ ማብራሪያዎችን በመስጠት የሕንፃው ስም አለመዞሩ ኦዲት ተደርጎ በጠቅላላ ጉባዔውም ላይ የተገለፀ በመሆኑ በዚህ ሰዓት በሊግ ካምፓኒው የመነሳቱ ግብ አጠያያቂ መሆኑን ገልፀዋል።

ሁለተኛ ጉዳይ የነበረው ሊግ ካምፓኒው ‘ፌዴሬሽኑ ለአንድ የሥራ አስፈፃሚ አባል አግባብነት የሌለው የጉዞ ወጪ አውጥቷል’ ሲል የወረፈበት ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ ተቋሙ ለሥራ ጉዳይ ግለሰቦችን ወደ ውጪ ሲልክ በተቻለ መጠን ወጪ በመቀነስ እና ከውስጥ ማኔጅመንቱ ጋር በመምከር እንደሆነ ያነሱት ፕሬዘዳንቱ “መግለጫውን ለሰጡት ሰው ትልቅ ክብር አለኝ። በእሳቸው ባይሆን ግን ጥሩ ነበር። ለእኔ በግሌ ‘በትኬት ጉዳይ ትታማለህ’ ብለው ነግረውኛል። መነሻ ሀሳቡ የእሳቸው ስላለመሆኑ ግን ስሜን የማውቀውን ያህል እርግጠኛ ነኝ።” በማለት ከእግርኳሱ ዙሪያ ሰላማዊ የሆነን ነገር መስራት ቢቻል ጥሩ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ፌዴሬሽኑ በሊግ ካምፓኒው የተወቀሰበት ሌላው ነጥብ ‘አምብሮ ከተሰኘው ትጥቅ አቅራቢ ጋር በገባበት ስምምነት ለአንድ ግለሰብ 200 ሺህ ብር ከፍሏል’ የሚል ነበር። ፕሬዚዳንቱ በሰጡት ምላሽ አምብሮ በነፃ ትጥቆችን ያቀረበበት ምክንያት ሀገሪቷ ካላት የገበያ ስፋት አንፃር መሆኑን ፣ በኮቪድ ምክንያት ውሉ ከአንድ ዓመት አልፎ ለሦስት ዓመታት መዝለቁን እንዲሁም
ፌዴሬሽኑ 12,500 መለያዎችን በማምጣት 10,000 የሚሆኑትን ለገበያ አቅርቦ ተጨማሪ የ10 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መስራቱን የተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማቀጠል ከኮሚሽን ክፍያ ጋር በተያያዘ ተቋማቸው ከመንግሥት የሚመደብለትን የአራት መቶ ሺህ ብር በጀት ከፍ ለማደረግ በዘረጋው የማርኬቲንግ ስትራቴጂ ግለሰቦች የስፖንሰርሺፕ ስምምነትን ለተቋማቸው ሲያመጡ እና ሲያስፈፅሙ እንደሚያመጡት የውል መጠን የሚወሰን (በቁጥር የተቀመጠ) የኮሚሽን ክፍያ እንደሚፈፀምላቸው በማስረዳት ከአምብሮ ጋር የነበረው የኮሚሺን ክፍያ አለመፈፀሙን በመጠቆም ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል። “ዶ/ር ሳሙኤል የሽዋስ የህክምና ክፍል ኃላፊያችን ከቡና ባንክ ጋር ሀሳቡን አመንጭቶ ፣ ምክረ ሀሳብ ቀርፆ ፣ ለፊርማ ጠርቶን በዓመት 18 ሚሊየን ብር አፈራርሞናል። ከዚህ ውስጥ 2.7 ሚሊየን ብር መውሰድ ነበረበት። ነገር ግን ነሐሴ 01 2013 ለእኔ ደብዳቤ ፅፎ ‘ገንዘቡ ለእግርኳስ ልማት እንዲውል ስለምፈልግ የኮሚሽን ክፍያውን አልወስድም’ በማለት 2.7 ሚሊየን ብር ለተቋሙ የተወውን ሰው ሁለት መቶ ሺህ ብር ሳይወስድ ወሰድክ በማለት መክሰስ ተገቢ አይደለም።” ብለዋል።

“በአጠቃላይ ፍሬ ነገሩ አሁን የምርጫ ጊዜ ነው። እኔ ለፕሬዘዳንትነት እየተወዳደርኩ ነው። ‘ገንዘብ ያለአግባብ ተጠቅሟል እና አትምረጡት’ ነው። ያሉት ፕሬዘዳንቱ ማብራሪያቸውን ቀጥለው ወደ ኃላፊነት ሲመጡ ፌዴሬሽኑ 16 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንደነበረበት እና ለሴካፋ ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች ውድድር ለመሳተፍ ሳይችል መቅረቱን በማስታወስ ከዚያ በኋላ ግን በስሩ የሚያደርጋቸውን ውድድሮች በመምራት ፣ ለክልል ፌዴሬሽኖች 12 ሚሊዮን ብር በመስጠት ፣ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማምጣት በርካታ ወጪዎችን ካወጣ በኋላ አሁን ላይ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ በአካውንቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“የሊግ ካምፓኒው ይህንን መግለጫ ስለሰጠ ከፌዴሬሽኑ ጋር ሆድ እና ጀርባ ይሆናሉ ብላችሁ እንሳታስቡ ፤ በፍፁም አይሆንም። ይሄ ሊግ አንድ ችግር ገጥሞት መንገድ ላይ ቢቆም ፊፋ የሚጠይቀው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን ነው።” ያሉት አቶ ኢሳይያስ ሊግ ካምፓኒው መግለጫውን ያቀረበበት መንገድ እና የተጠቀመውን ግለሰብ በተመለከተ ግን ቅር መሰኘታቸውን የሚጠቁም ሀሳብ ሰንዝረዋል። በተለይም ከመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ሆኖም በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያሉ ተገቢ ባልሆነ መንገድ መረጃ የሚሰጡ አካላት እንዳሳሳቷቸው እንደሚያምኑንም ተናግረዋል።

“በዚህ ደረጃ ጊዜያችሁን ባልወስድ ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን ህዝቡ ጋር የገባው አየር መልካም ስላልሆነ ሰዉ በአግባቡ መረዳት ስላለበት ነው።” በማለት ማብራሪያቸውን ያጠናቀቁት ፕሬዝዳንቱ ከጋዜጠኞች በተነሱላቸው ጥያቄዎች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ሰጥተው መግለጫው ፍፃሜውን አግኝቷል።