የዋልያዎቹ ተፋላሚ ስብስቧን ይፋ አድርጋለች

ነሐሴ 20 እና 29 በቻን የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ዋልያዎቹን የሚፋለመው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል።

በቀጣዩ ዓመት በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ በየቀጠናው የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተደረጉ እንደሚገኝ ይታወቃል። በሴካፋ ዞንም የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን ከቀናት በኋላ ደግሞ የሁለተኛ እና የመጨረሻ ዙር የደርሶ መልስ መርሐ-ግብሮች ይከናወናሉ። በመጀመሪያው ዙር ደቡብ ሱዳንን 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት የረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከቀናት በኋላ ከሩዋንዳ ጋር ለመፋለም ዝግጅቱን አዳማ ላይ እያከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነችው ሩዋንዳም በትናንትናው ዕለት ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረቧ ታውቋል። ስፔናዊው አሠልጣኝ ካርሎስ አሎስ ፌረርም ሦስት ግብ ዘቦች፣ ዘጠኝ ተከላካዮች፣ ስድስት አማካዮች እና ስድስት አጥቂዎች የመረጡ ሲሆን ከመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ከነገ በስትያ እሁድ ተሰባስበው ልምምድ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።

የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታ ነሐሴ 20 ታንዛኒያ ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ላይ ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ነሐሴ 29 ሩዋንዳ ሁዬ ስታዲየም ላይ ይደረጋል።

የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ከስር ተያይዟል 👇