ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና ተጠናቋል

በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና በክለቦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በክልሎች ኦሮሚያን አሸናፊ በማድረግ በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን አግኝቷል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አወዳዳሪነት በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አዘጋጅነት ከነሀሴ 1 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የ2014 የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና ሁለት የፍፃሜ ጨዋታዎች ተስተናግደውበታል።

በመዝጊያ ሥነ ስርአቱ ላይ አቶ ኢሳያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ፣ ወ/ሮ ሳሚያ አብደላ የኦሮሚያ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ፍሬው አሬራ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ተስፋዬ ሙላቱ የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ደመላሽ ይትባረክ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት እና አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ ክልል እግር እግኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው የፍፃሜ ጨዋታዎቹን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ቀደም ብሎ ረፋድ 3፡00 ሰዓት ሲል የፍፃሜ ተፈላሚ የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚው ነበር፡፡ ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን መመልከት በቻልንበት በዚህ ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ በተሰጠው የመለያ ምት የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ እዩኤል አለማየሁ የቅዱስ ጊዮስጊስ ተጫዋቾችን ሁለት የመለያ ምት መልሶ ጨዋታው በንግድ ባንክ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በክለቦች መካከል የተደረገውን ጨዋታም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሻምፒዮን መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

የመጀመሪያው የክለቦች የፍፃሜ ጨዋታ በጊዜ አለመጠናቀቁን ተከትሎ ዘግይቶ የጀመረው የቀይ ዛላ እና ኦሮሚያ ክልል ጨዋታ በኦሮሚያ ክልል የበላይነት ተደምድሟል፡፡ የተሻለ የሜዳ ላይ ንቃትን ይዘው የገቡት ኦሮሚያዎች ብልጫን ወስደው በተንቀሳቀሱበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ዮሴፍ ዳንኤል በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ያገኛትን ኳስ ከመረብ አሳርፎ ኦሮሚያን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ በዚህኛው የጨዋታ አጋማሽ የደቡብ ክልሉ ቀይ ዛላ ወደ አቻነት የመለሰኝን ግብ 30ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሪያለሁ ባለበት ቅፅበት የዕለቱ ረዳት ዳኛ በውጪው መረብ ሾልኮ ነው የተቆጠረው በማለት ተሽራለች፡፡ በዚህ መነሻነትም ቀይ ዛላዎች የዕለቱ ዳኛ ግብ ተቆጥሮ እያለ መሻር አልነበረበትም በማለት ክስ አስይዘው ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ የኦሮሚያው ፈጣኑ አጥቂ ዱንጂ ሀጂ ሁለተኛ ጎልን አክሎ ጨዋታው በኦሮሚያ 2-0 አሸናፊነት በመጠናቀቁ ክልሉ የ2014 በክልሎች መካከል የተደረገውን ውድድር ሻምፒዮን ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በዕለቱ የክብር እንግዶች የተለያዩ የሽልማት ስነ ሥርዐቶች ተካሂደዋል፡፡ አስቀድሞ ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች ፣ ድርጅቶች እና ተቋማት የሰርተፍኬት ስጦታ የተበረከተ ሲሆን ቀጥሎም የሜዳሊያ ሽልማት በክለቦች ደረጃ ወላይታ ድቻ ሦስተኛ ሆኖ በመፈፀሙ የነሀስ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የብር ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወርቅ እና የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን በክልሎች አዲስ አበባ ከተማ የነሀስ ፣ ቀይ ዛላ (ደቡብ ክልል) የብር እና ኦሮሚያ ክልል የወርቅ ሜዳሊያ እና የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የፀባይ ዋንጫ በክለቦች ለወላይታ ድቻ ለክልሎች ለአማራ ክልል ተበርክቷል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ከአሸናፊነቱ ዋንጫ በተጨማሪ ልዩ የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን በመጨረሻም ውድድሩን ላስተናገደው የሲዳማ ክልል የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቶ ሥነ ስርአቱ ተገባዷል፡፡