አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድናቸው ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኖ 0ለ0 ከተለያየ በኋላ ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።
ጨዋታው እንዴት ነበር?
“ይህ ጨዋታ በሁለት ቀን ልዩነት ያደረግነው ነው። ቢሆንም ለቀጣይ ጨዋታ ቡድናችንን በደንብ እንድናይበት ረድቶናል። በሁለት ቀን መካከል ሪከቨር ማድረግ ትንሽ ከባድ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ከሜዳው አንፃር ብዙ መጥፎ ነገር ነበር ማለት አልችልም። በተጨማሪም ዩጋንዳዎችም በጣም አትሌት ናቸው ፤ የጉልበት አጨዋወት ላይም ጠንካራ ናቸው። ይህንን ነገር ተቋቁሞ መውጣት ቀላል አይደለም። ከስነ-ልቦና አንፃር ራሱ ትልቅ ጥቅም አለው። ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ጥሩ ነገር ነው ያለው። በአምስቱ ጨዋታዎች ምንም ጎል አላስተናገድንም ፤ ሰባት ስምንት ጎል ገደማ በተቃራኒው አስቆጥረናል። ጥሩ መንገድ ላይ እንዳለንም ነው የማስበው። ለሩዋንዳውም ጨዋታ በበቂ ተዘጋጅተንበታል። የተወሰኑ ተጫዋቾችን እንዲያርፉ እና ከግጭት እንዲሁም ከጫና እንዲጠበቁ ለማድረግ ሞክረናል። በአጠቃላይ ሁለቱን ጨዋታዎች ጥሩ ተጠቅመንበታል።”
በሁለቱ ጨዋታዎች ቡድኑ ላይ ስለታየው ጠንካራ እና ደካማ ጎን…?
“የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ከተጋጣሚ የሚመጣውን ጫና መቋቋም ላይ ትንሽ ክፍተት ነበር። ዛሬ ግን ከሞላ ጎደል ከዛ የሚወጡበትን ነገር ለመሞከር ጥረናል። እንደዚህ አይነት ፈተና ነገ ቢገጥመን በተወሰነ ደረጃ ቀርፈን ለመውጣት ችለናል ብዬ አስባለው። ከዚህ ውጪ ከተጠቀምናቸው ተጫዋቾች እና ከሰጠናቸው ደቂቃ አንፃር ያለው ነገር በቂ ነበር ብዬ ነው የማስበው።”
በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ስላለው ክፍተት…?
“ማጥቃቱ መጀመሪያ ከመሰረቱ መስተካከል አለበት። በመጀመሪያው ጨዋታ 11 ገደማ የፈጠራ ደረጃ ላይ ገብተን ነበር። እነሱን ጥራት ማሳደግ ያስፈልጋል። በሁለቱ ጨዋታዎች መካከል ያለው አንድ ቀን ነው። ይሄንንም አንድ ቀን ለሪከቨሪ ነው የተጠቀምንበት ፤ ተጫዋቾቹን የነበረውን ነገር ከማውራት ውጪ ሜዳ ላይ ያሉ የእርማት ስራዎችን አልሰራንም። ስለዚህ ጨዋታዎቹን በነበረው መንገድ ነው የቀጠልነው። ቀጣይ ጨዋታ ግን እዚህ ጋር ያለውን ክፍተት የሚያርም ወይም የሚያሻሽል ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን። ግን ቀላል አይደለም በእነዚህ በርካታ ጨዋታዎች በምትጫወትበት መንገድ የተወሰኑ ዕድሎችን መፍጠር ከቻልክ እና እንዳይገባብህ ማድረግ ከቻልክ ቢያንስ ጥሩ መንገድ ላይ ነህ። ግን መታረም ስላለበት እርሱ ላይ እንሰራለን።”
የሁለቱ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ጥቅም…?
“የአቋም መፈተሻ ጨዋታው የተጫዋቾቹን የማች ፊትነስ የምንመለከትበት ነው። ከዚህ አንፃር ከአላዛር እና አማኑኤል ውጪ ሁሉም ሜዳውን እና ጌም ምን እንደሚመስል እንዲያዩት አድርገናል። በዋናነት የነበረን ፍላጎትም እርሱ ነው። ምናልባት ከሌላ ነገር ጋር ካያያዝነው በጨዋታው ማሸነፍ መሸነፍ ጋር ከመጣን ከሁለቱ ጨዋታ አንዱን አሸንፈናል ፤ ግን እርሱ ብዙ ጥቅም የለውም። ከእርሱ በላይ ተጫዋቾቹ ከመደበኛ ጨዋታ ከራቁ ከሁለት ወር በላይ ሆኗቸዋል ፤ ከሱዳን ጋር ካደረግነው የቻን ማጣሪያ ጨዋታ ውጪ። እንደዚህ እያረፍክ እየመጣህ መጫወትህ ደግሞ ተፅዕኖ አለው። ከዚህ አንፃር ተጫዋቾቹ የጨዋታ ዕድል እንዲያገኙ ማድረጋችን በቂ ነው።”
የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ስለነበረው ክፍተት…?
“እኛ ከምንጫወትበት መንገድ አንፃር ብዙ ጊዜ በተደራጁ ኳሶች ነው ማጥቃቶቻችን መሰረት ያደረጉት። ያንን ለማድረግ ደግሞ ብዙም ሜዳው የሚፈቅድ አይደለም። በተጨማሪም የእነርሱ የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥብቅ ነው ፤ በ9 ተጫዋች ምናምን ነው የሚከላከሉት። በጣም በሀይለኝነት እየተከላከሉ ሜዳውም እየረዳቸው ነበር። በዚህም የጎል ዕድል መፍጠር አልቻልንም። ግን አጋጣሚዎቹ አልነበሩም ማለት አይደለም። ወደ ጎል ዕድልነት መቀየር የሚችሉትን አጋጣሚዎች ከመቻኮል እና ከውሳኔ ስህተት ያመከናቸው ነበሩ። ምናልባት ጋቶች ከሩቅ የመታቸው ሁለት ኳሶች ከዛ የተሻሉ ሙከራዎች ማድረግ የሚቻልባቸው ነበሩ። እንደዚህ አይነት መጠነኛ ክፍተቶች አሉ ፤ ግን ይህ ከሜዳው እና ከተጋጣሚ አቀራረብ የመጡ ነበሩ።”
ከሚቾ ጋር ስላላቸው ወዳጅነት…?
“ሚቾ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ እኔ ገና የሰፈር አሠልጣኝ ነበርኩ። ልምምዶቹን ስለምከታተል ሰላዩ ነበር የምመስለው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በጣም ጓደኛዬ ነው። ጓደኛዬ ብቻ ሳይሆን መሪዬም ነው። ብዙ ነገሮች ላይ እርዳታው ሲያስፈልገኝ እደውልለታለው ፤ እርሱም እንደዚሁ። አፍሪካ ውስጥ ትልቅ ስራ እየሰሩ ካሉ ትልልቅ አሠልጣኞች ውስጥ አንዱ ነው። ለኳስ ያለው መሰጠት እንደምሳሌ ከምመለከታቸው አሠልጣኞች ውስጥ አንዱ አድርጎታል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ታሪክ አለው። በቀጣይም ጥሩ ነገር እንዲገጥመው እመኛለው።”