በሁለት ቀናት ልዩነት ዋልያዎቹን በአቋም መፈተሻ ጨዋታ የገጠመው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” ከዛሬው ፍልሚያ በኋላ አስተያየት ሰጥተዋል።
ጨዋታው እንዴት ነበር..?
“በቅድሚያ ይህን ከአፍሪካ ዋንጫ እና ዓለም ዋንጫ ማጣርያው ስብስብ አቡበከር ናስር እና ሽመልስ በቀለ የጎደሉትን ቡድን መግጠም ቀላል አይደለም ፤ ቡድኑ ግብፅን ማሸነፉ በራሱ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ። ለዚህም ውበቱ አባተ እና ተጫዋቾች ትልቅ አድናቆት ይገባቸዋል። ዋናው ነገር መሰል ሁለት ጨዋታዎችን ማድረጋችን ከ100 ልምምዶች በላይ ዋጋ አለው። ተጫዋቾች ምን እና እንዴት መጫወት እንዳለባቸው በደንብ የመመልከት እድል ያገኘንበት ነበር። ተጫዋቾች ከዚህ ልምድ ከተሞላ ቡድን ጋር ያላቸውን ሁሉ ሰጥተው በመጫወታቸው ላመሰግናቸው ይገባል። የኢትዮጵያ ቡድን ላለፉት አመታት ሳይበተን አብሮ የቆየ ነው። ለምሳሌ መስዑድ መሐመድ ለረጅም ዓመታት ሲጫወት አውቀዋለሁ ፤ እሱን ዛሬ መመልከቴ ቡድኑ እንዴት የካበተ ልምድ እንዳለው ይናገራል። እኛ ደግሞ ይዘነው ከመጣናቸው 22 ተጫዋቾች ወደ 11 የሚጠጉት ከ20 ዓመት በታች የመጡ ናቸው። ይህን ከግምት ስናስገባ መሰል ጨዋታዎችን ለእነዚህ ተጫዋቾች የመማርያ መድረክ ናቸው።”
በሁለቱ ጨዋታዎች ያቀዱትን ስለማሳካታቸው…?
“በሚገባ ፤ ዓለምአቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በዚህ ደረጃ ጥሩ ከሆነ ተጋጣሚ ጋር ከማድረግ የበለጠ ነገር የለም። ከጨዋታዎች ጥሩ በሆነ የፉክክር ከባቢ በነፃ ትምህርት እንደማግኘት ነው። ጨዋታውን ላመቻቸው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን እና ፕሬዘዳንቱን ኢሳይያስ ጅራን እንዲሁም አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ለማመስገን እወዳለሁ። ጨዋታዎቹ ነገሮችን እንድንሞክር እና እንድንማር እድል ሰጥተውናል። በቀጣይ የቀሩንን ነገሮች አርመን ለፉክክር ጨዋታው እንቀርባለን።”
ስላደረጉት እንቅስቃሴ…?
“የመጀመሪያው ጨዋታው ዕለት እኩለ ሌሊት ላይ ነበር የገባነው ፤ ይህም ተፅዕኖ አሳድሮብናል። ከዚያ ባለፈ የአየር ሁኔታው እና ሜዳው የራሳቸውን ተፅዕኖ አድርገውብናል። በተጨማሪም የገጠምነው ቡድን ጠንካራ መሆኑ በራሱ ትንሽ ፈትኖናል። በማጥቃቱ ረገድ በተለይ በሽግግሮች ወቅት የምናሻግራቸው ኳሶች በቂ ሰው ሳጥን ውስጥ አናደርስም ነበር። ይህም በቀሪዎቹ 7 ቀናት የምንሰራው የቤት ስራ ይሆናል።”
ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ያላቸው መልዕክት…?
“መልካም ሁሉ እንዲገጥመው እመኛለሁ ፤ ባለፉት 20 ዓመታት ጥሩ ወንድሜ ነበር። የዛሬ 20 ዓመት አዳማ ላይ ተገናኝተን ነበር። እኔ ጊዮርጊስን ይዤ እሱ ደግሞ የታዳጊዎች አሰልጣኝ ሆኖ ማስታወሻ ይዞ ተገናኝተን ነበር። በእነዚህ ዓመት በሚገባ ራሱን አሳድጓል። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። ትላንት ተገናኝተን ስናወራ በወቅቱ የተነሱ ፎቶዎች እያሳኝ ነበር። በወቅቱ የሀገሪቱ ምርጥ አሰልጣኝ እንደሚሆን ገምቼ ነበር። አሁን ባለበት ነገር ደስተኛ ነኝ ፤ ወደፊትም ትልቅ ነገር እንዲሰራ ከልቤ እመኝለታለሁ።”