በአሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው አዳማ ከተማ ከሌሎቹ የሊጉ ክለቦች ዘግይቶ ከነገ በስትያ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሊጀምር ነው።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መገባደጃ ላይ ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ተለያይቶ ምክትል አሠልጣኙ ይታገሱ እንዳለን በጊዜያዊነት የሾመው አዳማ ከተማ ከሳምንታት በፊት አሠልጣኙን ዋና አድርጎ ለከርሞ እንዲያዘልቀው በመንበሩ አስቀምጦ ነበር። ከሌሎቹ ክለቦች አንፃር ዘግየት ብሎ በዝውውር መስኮቱ የተሳተፈው ቡድኑም መስዑድ መሐመድ፣ ዊሊያም ሰለሞን፣ ሰዒድ ሐብታሙ፣ ቦና ዓሊ እና አድናን ረሻድን ማስፈረሙን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የሊጉ አዲስም ሆነ ነባር ክለቦች ከቀናት በፊት ልምምዳቸውን ማድረግ የጀመሩ ሲሆን አዳማ ከተማ ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እስካሁን ዝግጅቱን ሳይጀምር ቆይቶ ነበር። አሁን ባገኘነው መረጃ መሠረት ግን በትናንትናው ዕለት ለቡድኑ ተጫዋቾች ጥሪ የተላለፈ ሲሆን በነገው ዕለት በመቀመጫ ከተማው አዳማ ተጫዋቾቹ ተሰባስበው በማግስቱ ማክሰኞ የህክምና ምርመራ አከናውነው ዝግጅታቸውን ዝዋይ ላይ በመከተም ይጀምራሉ። ይህም ከሁሉም ክለቦች ዘግይቶ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረ ክለብ ያደርገዋል።