👉”ምርጫውን መቀበል ግዴታ ነው። ከግለሰብ ፍላጎት ይልቅ የሀገር ጥቅም ስለሚበልጥ ምርጫው ፍትሃዊነቱን ጠብቆ ሲመጣ እርሱን መቀበል ግድ ነው የሚሆነው”
👉”ስንመጣ 150 ሺህ ብር ነበር ስንሸልም የነበረው አሁን የሊግ ካምፓኒው ወደ 12 ሚሊዮን ብር ያደረሰበት ውሳኔ አካል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ”
👉”እኔ ሰራተኛ ነበርኩ ፤ አሁንም ሰራተኛ ነኝ። ባለሀብት አይደለሁም። ባለሀብት ካልሆንኩ እኔን ለምን በገንዘብ ትጠረጥረኛለህ?”
👉”በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት የጉባኤውን አባላት ደህንነት የመጠበቅ ሀላፊነት አለብን”
👉”የጉባኤው አባል የራሱን ክብር ያውቃል ፤ ስራውን ያውቃል ፤ ማንን እንደሚመርጥም ያውቃል”
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና የስራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ባለንበት ሳምንት መጨረሻ እንደሚደረግ ይታወቃል። ለፕሬዝዳንትነት ከሚወዳደሩት ግለሰቦች መካከል አቶ መላኩ ከትናንት በስትያ ቀድመው መግለጫ የሰጡ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የወቅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ እና ሌላኛው ተወዳዳሪ አቶ ቶኪቾ መግለጫ ሰጥተዋል። በቅድሚያም ቀትር ላይ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለሁለት ሰዓት የቆየ መግለጫ በስካይ ላይት ሆቴል ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ በቅድሚያ ባለፉት አራት ዓመታት የተሰሩትን ስራዎች በማንሳት ንግግራቸውን ጀምረዋል።
“እንደሚታወቀው የዛሬ አራት ዓመት ወደዚህ ስመጣ እንዲሁ የተዘጋ ምንም ስራ ያልሰራ ተቋም አይደለም የተረከብነው፡፡ ረጅም ጊዜ የቆየ ብዙ ተደክሞበት እዚህ የደረሰ ተቋምን ነው የተረከብነው ፤ ከዚህ በፊት ለነበሩት አመራር ትልቅ ክብር ነው ያለኝ። ብዙ ጊዜ አይለመድም የሰራውን ሰው ማመስገን እና ብዙ ለፍተው እዚህ ያደረሱትን አስተዋጽኦ ትቶ አዲስ ጎጆ እንዳልገነባን መታወቅ አለበት። ሆኖም ግን ስንመጣ የራስ አስተሳሰብ ይኖራል። ክፍተቶች ይኖራሉ ታያለህ እነርሱ ላይ ለመስራት የሪፎርም ጥናት ስራዎችን አካሂደን ክፍተቶቹን ለመሙላት ጥረት አድርገናል፡፡ እግር ኳስ ሜዳ ላይ የነበሩ አስደንጋጭ ግጭቶች ፣ ሽኩቻዎች የነበሩበት ነበር። በጣም ፈተና የነበረበትን ነገር ለማስተካከል የሮጥንበት ጊዜ ነው የነበረው፡፡ የዛሬ አራት ዓመት የነበራችሁ ሰዎች ኢሊሌ ሆቴል ስትራቴጂክ ፕላን አውጥተን ሳናቀርብ ብንመረጥ ምንድነው የምናደርገው ብለን የተወሰኑ ነጥቦችን አንስተናል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የሊግ ምስረታው ነው፡፡ ክለቦች የራሳቸውን ውድድር እንዲመሩ የማድረግ ስራን የሰራንበት ከዛ በኋላ ደግሞ የተመሠረተው አካል የሄደበት ርቀት በጣም ክሬዲት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዓለም ላይ ወጥቶ ገንዘብን ማምጣት የጀመረበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ስንመጣ 150 ሺህ ብር ነበር ስንሸልም የነበረው አሁን ዛሬ የሊግ ካምፓኒው ወደ 12 ሚሊዮን ብር ያደረሰበት የዚህ ውሳኔ አካል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። ብዙዎቹ ክሬዲቱን ለፌዴሬሽኑ ነው መስጠት የሚፈልጉት በግልፅ ለሰራው ሰው ዕውቅና መስጠት ስለሚያፈልግ የወሰነው ውሳኔ ክለቦቹ ውድድራቸውን እንዲመሩ የፌዴሬሽኑ አመራር የወሰነው ውሳኔ መነሻ ነው። ካምፓኒውን እንደ ኮሚቴ አቋቁመን የሰራነው ስራ ነው። በእርግጥ ይሄን ስንሰራ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ሸበሌ ሆቴል ባለሙያዎችን አሰባስበን ረጅም ጊዜ ጥናት ተደርጎ እሱን ጥናት ለክለቦቹ ለማብራራት እና ለማሳመን በራሱ ፈተና ነበር የነበረው። በእዛ ውስጥ አልፈን ዛሬ እዚህ ደርሶ በአጭር ጊዜ ፍሬ አፍርቷል፡፡ በዚህ ዙሪያ ለሰሩት ሰዎች በሙሉ ትልቅ ክብር ነው ያለኝ። ከዚህ ባለፈ ተቋሙ የተደራጀ የራሱ ሔድ ኳርተር አልነበረውም ይሄንን ማሳካት ችለናል።” ካሉ በኋላ ከብሔራዊ ቡድኖች ጋር የተሰራውን ስራ ማብራራት ይዘዋል።
“ብሔራዊ ቡድኑ ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስ ችሏል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገን ነው የሰራነው። ሴቶች ብሔራዊ ቡድኖቻችን በሁሉም የዕድሜ ደረጃ ያሉት ከ17 ዓመት በታችም ከ20 ዓመት በታችም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከጫፍ ደርሰው የወደቁበት፣ ከ20 ዓመት በታች የምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን ያነሳበት፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰበት አሁን ደግሞ ከምድቡ በጎልም ቢሆን አንደኛ ሆኖ ያለበት እንዲሁም ታሪካዊ አሸናፊያችን ግብፅን ማሸነፍ የቻለ ብሔራዊ ቡድን የተገነባበት ጊዜ ነው የነበረው፡፡”
አቶ ኢሳይያስ ከብሔራዊ ቡድኖቻችን ስኬቶች በኋላም ከወጣቶች እግርኳስ ጋር የተገናኘ ሀሳብ አንስተው ሌሎች ተሰርተዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ዳሰዋል። ” የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ትልቁ ክፍተቱ ክለብ ላይሰንሲንግ መሬት አድርሶ መስራት አለመቻሉ ነው። ወደፊት እነግራችኃለው፡፡ ይሄን ነገር ስትመልስ የወጣት ልማት ስራውን ክለቦቹ በስራቸው ማደራጀት እንዳለባቸው የሚያስገድድ ስርዐት መሰረተ ልማትም ስታዲየም ባይገነቡም በኪራይ እንዲኖራቸው ግልፅነት እና ተጠያቂነት ያለበት የፋይናንስ ስርዐት መዘርጋት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነገር የለም። በዚህ ላይ አልሰራንም። ይሄ ሲመለስ ነው የወጣት ልማት ስራው አብሮ መልስ የሚያገኘው። ስለዚህ ይሁን ብለን ፓይለት ፕሮጀክት ጀምረናል። ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት ከ15 ዓመት በታች በወንድም በሴትም አንድ ሺ አካባቢ የሚደርሱ ህፃናት ናቸው የነበሩት፡፡ ይሄ ጠብታ ነች ማለት ነው። ይሄንን እንደ ምሳሌ ወስዶ በሁሉም ደረጃ ያሉ ክለቦቻችን መስራት አለባቸው ነገር ግን እሱ ተስፋ የሚሰጥ ነው። በዚህ ደረጃ መስራት ከተቻለ ወደሆነ ቦታ መድረስ እንችላለን ብለን ነው የምናስበው፡፡
“ፋይናንሳችን በጣም ደካማ ነበር። ኔጌቲቭ ውስጥም ነበር የነበርነው። ይሄን በተደጋጋሚ አንስቼያለሁ፡፡ ፋይናንስ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሰርቶ አሁን መልካም ቁመና ላይ መቆም ተችሏል። ይሄን ሁሉ እየሰራን ብሔራዊ ቡድኑ ሜዳ አጥተን ከሀገር ውጪ ሄደን እየተጫወትን ለዚህ ትርፍ ብር እየከፈልን የአውሮፕላን ትኬት ፣ የሜዳ ኪራይ ወጪ እየከፈልን እነኚህን ሁሉ ወጪዎች እያስተናገድን ከ17 ዓመት በታች ፣ ከ20 ዓመት በታች በወንድም በሴትም ፣ የሴቶችን ሊግ ፣ ከፍተኛ ሊጉን፣ ብሔራዊ ሊጉን በፌዴሬሽኑ ወጪ ከአድምንስትሬሽን ወጪ ቀንሰን እያስተናገድን ዛሬ መልካም ላይ ነው። ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ አካውንት ውስጥ ለማስተላለፍ ተዘጋጅተን ነው ያለነው። የሚመጣው አካል አቅዶ መስራት የሚችልበት መነሻ እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል።
“ሌላው የካፍ አካዳሚ ትልቅ ጫካ የነበረው ፤ 13 ዓመት ሙሉ ተዘግቶ ነበር ነገር ግን አርባ ክፍል አርባ አልጋ ተነጥፎ ቁጭ ብሎ ሆቴል እንከራይ ነበር እና ያን ወደ ስራ ማስገባት የተቻለበት የህዝብ ግንኙነት ስራው መልካም ነው ተደራሽ መሆን ችሏል፡፡ ዌብሳይቱ እኛ ስንመጣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አሸናፊ በቀለን አሰልጣኝ አድርጎ ቀጠረ ይላል። አሸናፊ በቀለ ግን ከለቀቁ ቆይተዋል። ስለዚህ እሱን አብዴት ማድረግ ስላለብን ባለሙያዎች በዚህ ዙሪያ እንዲሰሩ የአይቲ ሲስተማችንን አጠናክረን ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች ላይ ጭምር በዲጂታል ቴሴራ የአንዱን ሊቆጣጠር በሚቻልበት ስርዐት አጠናክረን የምንቀጥልበት ስራ ነው የነበረው። በአጠቃላይ እንደው በግርድፉ ስናይ የመጀመሪያውን ዓመት ሳንጨምር ሶስቱን ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን መልካም ጉዞ አድርጓል ብሎ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከእዛ ውጪ ክፍተት አለብን ምን ላይ ነው ትኩረት የምታደርገው በአጭሩ የምትሉ ከሆነ ሪፎርም ቀጣይም የሚቀጥል ነገር ነው አንዴ ሰርተህው የምታቆመው አይደለም እና ተቋማዊ አደረጃጀታችን የአራት ዓመቱን ገምግመን መልካም ቁመና ላይ እንዲደርስ እሱ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡
” ስለ ክለብ ላይሰንሲንግ ማውራት ከጀመርን ቆይቷል። እዚህ ጎረቤታችን ዩጋንዳ መልካም ነገር ላይ ነው ያለችው። በዚህ ነገር ግን እኛ አንድ ደረጃም አልሄድንም፡፡ ይሄ ውስጣዊ ተፅእኖዎም አለው። ወደድንም ጠላንም በዚህ ሀገር ውስጥ አንድን ተቋም ስትመራ ሀገራዊ ጉዳዮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅእኖ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ መጀመሪያ የለውጥ ሂደቱ ሀገራዊ ከዛ በኋላ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ከዛ በኋላ እሱን ሰባት ወር ስምንት ወር ስፖርተኞቹ ወደ ቤት ከተመለሱ በኋላ የሀገር ውስጥ ግጭት ጉዳይ እነኚህ ስፖርቱ ላይ በቀጥታ ተፅእኖ ያደርጋሉ። ለምን ክለቦቻችን በመንግስት የሚተዳደሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በጀት የሚያገኙት በየደረጃው ካለ ተቋማት ነው፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ስርዐት ለመምጣት ተፅእኖ ያደርጋል እና ይሄን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ችግር ነበረብን። በቁርጠኝነት ልንሄድበት ያልቻልነው እና መስተካከል የሚገባው ስራ ይሄ ስለሆነ እዚህ ላይ ቢያንስ ከሊግ ካምፓኒው ጋር ተቀራርበን በመስራት ቢያንስ በ16ቱ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ላይ ይሄን ተግባራዊ ለማድረግ እንሰራለን፡፡ ካፍ አካዳሚን ወደ ተሻለ ደረጃ ማስፋት እናስባለን። በእጃችን ላይ ያለው ካፍ አካዳሚ ውስጥ ያለውን ነገር ለማሳደግ ባለፉት አራት ዓመት ውስጥ ሰርተን ማስረከብን አላማ አድርገን ነው እየተንቀሳቀስን የነበረው። ይሄ ቢሳካልኝ የእኔ ትልቁ ስኬቴ ነው፡፡ ፕለይ ግራውንድ ሊኖረው ይገባል። ከእዛ ውጪ እሱ ጊቢ ገቢን ማስገኘት አለበት፡፡ እዚህ መሀል ከተማ ያለው ህንፃ ሌላ ስራ ሰርቶ የፌዴሬሽኑ ተቋም ራሱ ተቋማዊ አደረጃጀቱ አካዳሚው ቦታ ላይ ትኩረት ያደረገ ገቢ የሚያስገኝ አንድ ተቋም መፍጠር አለብን ብለን የምናስበው፡፡ ይሄን ከመንግስት ጋር በቅርበት ተቀራርበን ሰርተን ሙሉ በሙሉ ወደ እኛ ካዞርን በኋላ ፊፋ በዚህ ላይ ፕሮጀክት አለው ከፊፋ ጋር ሰርተን ወደ ተሻለ ቦታ እንወስዳለን የሚል ህልም ነው።
“ሌላው የእኛም የፊፋም ትኩረት የብሔራዊ ቡድን ግንባታ ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድን ስናወራ የሲኒየር ብሔራዊ ቡድኑን ብቻ አይደለም። ብሔራዊ ቡድን ብሔራዊ አርማችን ነው፡፡ በሁለቱም ፆታ በዕድሜ ደረጃ ያሉ ብሔራዊ ቡድኖች እነርሱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለባለሙያዎች ጊዜ ሰጥተን ሥራ መስራት ጀምረናል፡፡ ሶስት ሁለት ወር የነበሩ ኮንትራቶችን ወደ አንድ ዓመት አሳድገናል እና እሱን በደንብ እየሰጠን የብሔራዊ ቡድን ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድን ስንገነባ የወዳጅነት ጨዋታዎች በአግባቡ መጠበቅ ጀምረናል። እነርሱ ወደ ኋላ መመለስ የለባቸውም እዚህ ላይ በደንብ የምንሰራው ጉዳይ ነው፡፡
“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የምርጫ ሂደት ለሌሎች ለሀገራችን ምርጫ ምሳሌ መሆን የሚችል መሆን አለበት፡፡ ከአዳራሽ ውጪ ያለውን ጨዋታ አላውቅም። ከእናንተው እሰማለሁ አዳራሽ ውስጥ ከተገባ በኋላ ግን ትራንስፓራንቲ የሆነ የሚያሳይ ሳጥን ከፊት ለፊትህ ይደፋል ከዛ የሚነሳው ሰው መጥቶ ቦክስ ውስጥ የራሱን መምረጥ የሚፈለገውን መርጦ ቦክስ ውስጥ ያስገባል፡፡ ስለምንድነው እዚህ ምርጫ ላይ ስለማጭበርበር የሚነሳው። የማይመጡ ነገሮች አይመጥኑንም ፤ ለህዝብ ጆሮ የማይመጥኑ አይመጥኑም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ምሳሌ ሊሆን መቻል አለብን፡፡ የጉባኤው አባል የራሱን ክብር ያውቃል ስራውን ያውቃል ማንን እንደሚመርጥ ያውቃል። አንድ ሰው በሚፈጥረው ጫና የሚመርጥ ነው ብዬ አላስብም ምን እንደሚያደርግ ስለሚያውቅ፡፡ እኔ በዚህ በኩል የጉባኤውንም ክብር መንካት ባይቻል ጥሩ ነው፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል። በመጨረሻ የሱፐር ሊግ ፣ ብሔራዊ ሊግ እና የሴቶች ሊግ ክለቦቻችን የፊፋ ፕላስ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀው ሰፊ ማብራሪያቸውን አገባደዋል።
በስፋራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ያቀረቡት ጥያቄ እና አቶ ኢሳይያስ ጂራ የሰጡት ምላሽ
ለፋሲል ከነማ እና ጅማ አባ ጅፋር ፌዴሬሽኑ ገንዘብ ስለማበደሩ…?
እኔ ተቋሙን ስመራ ከኋላዬ 10 ሰው አለ። አስሩ ሰው ካልተገኘ አብላጫ ድምፅ ገዢ ነው። ገንዘቡን ስናበድር በሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ ነው። እንደውም ተነስታችሁ ልታጨበጭቡልን ይገባ ነበር ፤ ክለቦቹ ምን ሆነው ነው የተበደሩት የሚለውን በማንሳት። ወቅቱ በጀት የተዘጋበት እና መንግስት ያልተለቀቀበት ነበር። በዚህ ሁኔታ ነው ወደ ውድድር ለመሄድ እየተዘጋጁ የነበሩት። ደሞዝ መክፈል ስላልቻሉ ፊፋ አንዱን 1.2 አንዱን ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ብሎ ያስገደደው። እንደውም ክለቦቹ ወደ ግለሰቦች እና ሀብታም ተቋማት አይደለም የሄዱት። ‘የእኔ ተቋም ነው ፤ የእኔን ችግር ይረዳል’ ብለው ነው ወደእኛ የመጡት። ይሄንን በጥሩ ጎኑ አይተን ፊፋ የቀጣውን ቅጣት እንዲከፍሉ ነው ገንዘቡን የሰጠናቸው። አንዱ እንደውም ሲመልስ ከምስጋና ደብዳቤ ጋር ነው። የማበደሩ ስልጣን አላችሁ ከሆነ ጉባኤው ስልጣን ሲሰጠኝ በጀትም እንዳስተዳድር ሀላፊነት ሰጥቶኛል። በዚህ አግባብ ነው ያደረግነው። አይደለም በዚህ ደረጃ ሀገርን ወክለው ለሚሄዱ ክለቦች ይቅርና ትናንትና ለሀገር ብዙ ለፍተው አሁን ችግር ላይ ለወደቁ ብዙ ዜጎቻችን ደርሰናል። ይሄንን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መስማት እኮ ህልም ነው የሚመስለው። ከጎዳናም ሰው አንስተናል። አሠልጣኝ ሆነው ታመው የአልጋ ቁራኛ የሆኑትን ቤት ድረስ ሄደን ጠይቀን ድጋፍ አድርገናል። በኮሮና ጊዜም ስታዲየም ዙሪያ ያሉ ወገኖቻችንን ሰብስበን ለ5 እና 6 ወር ከሌሎች ተቋማት ጋር ሆነን ስንሰራ ነበር። ስለዚህ አመራሩ በዚህ ሙሉ መብት አለው። ባደረግነውም ነገር ደስተኞች ነን። ክለቦቹም ደስተኞች ናቸው። ‘እውነትም ለእኛ የሚያስብ ተቋም አለን’ ብለው እንዲያስቡ ሆኗል። ለጅማ ለማበደር ብሎ ፋሲልን ከአጠገቡ አስቀመጠ የሚባለው ስሜት አይሰጥም። ተነጋግረውም አይደለም የመጡት። መጀመሪያ እንደውም ፋሲል ነው የመጣው። ይሄንን ካልመራው እኔ እዚህ ቦታ ምንድን ነው የምሰራው ታዲያ? ቡድኖቹ ከውድድር ይቅሩ? ይሄንን ማየት ያስፈልጋል።
ከፌዴሬሽኑ ቴልኒካል ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ጋር ተያይዞ ስለሚነሱ ጉዳዮች…?
በመጀመሪያ ወደዚህ ስንመጣ የሪፎርም ጥናታችንን ካጠናን በኋላ የሰራተኞችን ቅጥር እኛ አልሰራንም። ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ አንጋፋ የስፖርት ክፍል አለው ፤ ምሁራን አሉበት። 98 ሺ ብር ከፍለን ክራይቴሪያ አውጥተው ሰራተኛ እንዲቀጥሩልን ለእነርሱ ነው የላክነው። አውትሶርስ አድርገን ነው የቀጠርነው። ቴዎድሮስ ተወዳድሮ ሁለተኛ የወጣ ግለሰብ ነው። በእሱ ቦታ አንደኛ የወጣው ሰው ከጉዞ ጋር ተያይዞ በተነበ ችግር ጠፋ። ስለዚህ በዛ ቦታ ሁለተኛ የወጣውን ልጅ እኛ ነን የጠራነው። ስንቀጥረው ቴክኒካል ዳይሬክተር ቦታ ላይ አይደለም። የቴክኒካል ዳይሬክተር ሰውዬው ስራውን ለቆ ሲወጣ ካሉት ሰራተኞች ብቃቱ በጽሕፈት ቤት በኩል በቀረበው መሰረት የሥራ-አስፈፃሚው ገምግሞ ነው በጊዜያዊነት የቴክኒክ ዳይሬክተር ያደረግነው። አሁን እኔ የምመልሰው እስከዚህ ደረጃ ነው። እሱ ‘ከፕሬዝዳንቱ ጋር መስራት ባለመጫሌ ነው የሄድኩት’ ብሎ መግለጫ መስጠት ይችላል። በአጋጣሚ ከአንድ ቀን በፊት መልካም ምኞት ለመመኘት ደውሎልኝ ነበር። በተረፈ ማንም መግለጫ መስጠት ይችላል። እርሱም እንደዛው።
በፉክክሩ ላይ ገንዘብ ይቀርባል ስለመባሉ…
እኔ ሰራተኛ ነበርኩ። አሁንም ሰራተኛ ነኝ። ባለሀብት አይደለሁም። ባለሀብት ካልሆንኩ እኔን ለምን በገንዘብ ትጠረጥረኛለህ? ሀብታሙ ሁሉ ይጠረጣል ማለትም አይደለም። አለውና ሊሰጥ ይችላል ብለህ ልትገምት ትችላለህ። እኔ እዛ መንደር ውስጥ አይደለሁም። በጣም ግልፅ፣ ያመንኩበትን የምናገር እና እጅግ በጣም ሰው የማከብር ሰው ነኝ። ስለራሴ ብዙ ማለት ባልፈልልም እንደዚህ የቆሸሸ ቦታ የሚውል ስብዕናም የለኝም። ያነሱት ግለሰብ መረጃ ካላቸው በመረጃ እገሌ ነው ማለት ይችላሉ። የቴክኖሎጂ ዘመን ስለሆነ በብዙ ነገር መያዝ ይቻላል። እሳቸው እንዳሉት አሁን ወሬዎችም እሰማለው። በተጨባጭ ግን ይሄ ነው ብሎ የሚያመጣልህ ሰው የለም።
የጠቅላላ ጉባኤው ቦታ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ስለመቀየሩ…?
ምርጫውን የማስተዳደር ስልጣን ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው። ምርጫውን የማስፈፀም ስልጣን ያለው ደግሞ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ነው። ዕድሉን ስንሰጥ ምንም ሳይባል ቦታውን ስንቀይር የሀገር መግለጫ ጋጋታ መጣ። ጎንደርንም የመረጠው ስራ አስፈፃሚው ነው። እኛ መጀመሪያም ዕድሉን የሰጠነው ለከተማው ነው። ከተማውን ደግሞ የሚያስተዳድረው መንግስት ነው። ከመንግስት አካል የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን የሚያሳዩ ማሳያዎችን አየን። አንደኛው የውስጥ ማስታወሻ እንደውም የክተት ጥሪ ነው የሚመስለው። ስለዚህ በመተዳደሪያ ደንባችን መሰረት የጉባኤውን አባላት ደህንነት የመጠበቅ ሀላፊነት አለብን። ለምሳሌ ጎንደር መሐል ከተማውም ባይሆን በጦርነቱ ገፈት ከቀመሱ እና ኢኮኖሚካሊ ችግር ውስጥ ከገቡ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። እነኚ ሁሉ አካላት ሳያውቁ እኮ ነው ጎንደር ከተማ ላይ ለ20 ዓመት በታች ውድድር 10 ቡድኖችን ልከን ከ2 ወር ያላነሰ ቆይታ ያደረጉት። ይሄ ድባቴ ውስጥ የገባውን የከተማ ኢኮኖሚ የመንቀሳቀስ ሥራ ነው። ለሁለት ቀን ስብሰባ የከተማውን ኢኮኖሚ ጎድታችሁ አመጣችሁ ይባላል። ለምን እንደሆነም አላውቅም። ስብሰባውን የሚያስተዳድረው ደግሞ ይሄ አካል ነው። የስብሰባው ቦታ ወደዚህ መጣና ተወዳዳሪው ላይ ምን ተፅዕኖ ያመጣል? ስብሰባውን ትራንስፖርት ከፍሎ የአዳራሽ ኪራይ እና የአበል ወጪ ሸፍኖ የሚያስተዳድረው እኮ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው። አንተ በምትመራው እና በምታስተዳድረው ስብሰባ እዚህ ቦታ ማካሄድ አለብህ ይባላል። ያለውን ነገር ለማጣራት ሰው ሁሉ ልከናል። ግን ከዛ በኋላ የሚመጡ መልዕክቶች ጥሩ አይደሉም። አንድ ግለሰብ ነው ብላችሁ ይሆናል ግን አመራር ነው ደውሎ የሚያስፈራራው። አመራርን እንደ አንድ ግለሰብ እንዴት ነው የምታየው። ጊዜ መውሰድ እና መነጋገር አትችሉም ለሚባለው አዎ ጠባብ ነበር ጊዜው። ይሄ የሚያስኬድ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ሀሳብ ገብቶን ነው።
እኛ ጎንደር የሴኩሪቲ ችግር አለ አይደለም ያልነው። በአካል ምርጫውን መጥቼ እበጠብጣለው ያለ አመራር ነው የደወለልን። ይሄንን ነው ያልነው። አመራሩን ደግሞ እንደ ግለሰብ አናየውም። የእኛ አመለካከት እማ ቅድም እንዳልኩት ክለቦች ተፈራርመው ወደዛ አንሄድም ብለው ያመጡ ጊዜ ከ20 ዓመት በታች 10 ቡድን ልከናል። ከዚህ ውጪ ነገሮችን ቅርንጫፍ ባናወጣባቸው ጥሩ ነው።
ሁለቱን ተወዳዳሪ እጩዎች እንዴት ያይዋቸዋል…?
ጥሩ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። እግርኳሱን ለማገዝ በቁርጠኝነት ለማገዝ እየተወዳደሩ ናቸው። ከሰው ጋር ለማነካካት ጥያቄ መቅረፅ አያስፈልግም። ምክንያቱም ማንም ኢትዮጵያዊ ለዚህ ቦታ መወዳደር ይችላል። በጣም መልካም ኢትዮጵያዊን ፤ ይሰሩ በነበሩበት ኢንዱስትሪ ላይ ውጤታማ የነበሩ ናቸው። ነገርግን እዚህ ኢንዱስትሪ ላይ ውጤት ያመጣሉ ወይ ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ ጉባኤው ይመልሰው። እኔ ለምንድን ነው ዘመቻ የምከፍተው።
ስለምርጫው ፍትሀዊነት…?
የምርጫውን ፍትሀዊነት የሚያረጋግጠው ምርጫ አስፈፃሚው ነው። በፍትሀዊነት እያካሄድኩ ነው ብሎ መግለጫ ሊሰጥበት ይችላል። ይሄ የሌላ አካል ስራ ነው። እኔ ተወዳዳሪ ነኝ። ፍትሐዊነቱን እንዴት ታየዋለህ ከሆነ ግን እናንተም እንምትሰሙት እኔም የምሰማቸው ነገሮች አሉ። አንድ ደግሜ የማረጋግጥላችሁ ነገር ቢኖር ሰው አዳራሽ ውስጥ ከገባ በኋላ የማንም ጣልቃ ገብነት እና ጫና ሳይኖር ይመርጣል። ስለዚህ ፍትሀዊ አይደለም ለማለት በዛን ቀን ተገኝቶ ማየት ያስፈልጋል። እኔ እስካየኋቸው ድረስ ግልፅነት የተሞላበት ስራ ነው የሚሰሩት። ከአዳራሽ ውጪ ያለ ነገር ያሰጋሃል ወይ ለሚለው ከአዳራሽ ውጪ ያለው ወሬ ነው ፤ ወሬ ደግሞ አያስፈራኝም።
የእኔ ስልጣን የሚያበቃው ጠቅላላ ጉባኤው ተሰብስቦ የሚቀጥለውን አመራር በመረጠ ዕለት ነው። ማታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ታንዛኒያ ከማቅናቱ በፊት ሆቴላቸው ሄጄ መልካም ዕድል ተመኝቼ ነው የመጣሁት። ምክንያቱም ሥራዬ ስለሆነ። ያለንን ሀብትም ከአግባብ በላይ ነው እየተጠቀምን ያለነው። ማሳያም ተቋሙን ከኔጌቲቭ 16 ሚሊዮን አውጥቼ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲኖረው አድርጌያለው። ይሄንን ያመጣነው ዝምብለን በትነን ሳይሆን ቆጥበን በሀላፊነት ስለተጠቀምን ነው።
ካልተመረጡ ምን ያደርጋሉ…?
እኔ ብሸነፍ 78 ገፅ ያለው ሌጋሲ ዶክመንት አዘጋጅቻለው። በ30 ደቂቃ ሥራ አላስረክብም። በ4 ዓመት ውስጥ ምንድን ነው የተረከብነው፣ ምንድን ነው የሰራነው፣ ክፍተታችንስ ምንድን ነው የነበረው እንዲሁም በቀጣይ ምንድን ነው መሆን የሚገባው የሚለውን አዘጋጅተናል። በዚህ ደረጃ ቀጣይ የሚመጣውን ሰው ከነክፍተቱ ተቀብለን እዚህ አድርሰናልና ፤ የሚቀሩንን ስራዎች የእርሶን ሀሳብ ጨምረውበት ተቋሙን አሻሽሉ ብዬ ሰነዱን ሰጥቼ የእኔን ምክር በሚፈልጉበት ሰዓት እየተነጋገርን የሀገሪቱን እግርኳስ ወደተሻለ ደረጃ ለማምጣት የራሴን የሆነ አስተዋፅኦ አደርጋለው። ምርጫውን መቀበል ግዴታ ነው። ከግለሰብ ፍላጎት ይልቅ የሀገር ጥቅም ስለሚበልጥ ምርጫው ፍትሃዊነቱን ጠብቆ ሲመጣ እርሱን መቀበል ግድ ነው የሚሆነው።
ከታክሲዬ ጋር ስለሚገናኝ ጉዳይ…
ይሄንን ጉዳይ ባለፈው መግለጫ ላይ በጣም ተቆጥቤ ነው ያለፍኩት። ምክንያቱም ቀጥተኛ ተወዳዳሪ ስለሆኑ ተፅዕኖ እንዳያመጣባቸው በሚል። ነገርግን መታወቅ የሚገባው ውል ገባን በአጋጣሚ ድርጅቱ የእርሳቸው ነው። ሦስት መኪና በየዓመቱ ይላል ፤ ተው ይሄ ነገር ይበዛል አልን። በ4 ዓመት 12 መኪና ማለት ነው። ህንፃው ራሱ ፓርኪንግ የለውም አይችልም። መኪና የሚሰጥህን ሰው እምቢ ባይባልም ተው ይበዛል ብዬ ነበር። ውሉን እኔ አይደለም የሰራሁት የማርኬቲንግ ዲፓርትመንቱ ሲያመጣው አልተሳሳታችሁም ወይ ብያቸው ነበር። መጨረሻው ግን አልሆነም። ዝርዝር ነገሮችን ማውራት አልፈልግም ፤ ምክንያቱም የሚይዙኝ የግል ስብዕናዎች ስላሉኝ ነው። ጉዳዩ ወደ ህግ ሄዷል። በውሉ መሰረት የመጀመሪያውን ክፍያ 1.8 ሚሊዮን ብር ከፍለውናል። ለእርሱ እናመሰግናለን። የቀረውንም ብር እንጠይቃለን። የቀረውንም መኪኖቻችን እንጠይቃለን።
የውድድር ሜዳዎችን በተመለከተ…
እኔ ስታዲየሞችን እሰራለው አልላችሁም። አሁን ስታዲየም የሚሰራበት በጀት ከፍ ብሏል ፤ በቢሊዮን ነው። ስታዲየም እገነባለው ብሎ ቃል መግባት የዋህነት እና ሰውን ማታለል ነው የሚሆነው። ቢሆንን ቢሆን የተጀመሩ ስታዲየሞችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲጨርስ እንሰራለን። ይሄንንም እያደረግም ነው። የአዲስ አበባ ስታዲየም ሲታደስ በፌዴሬሽኑ ወጪ የኦሎምቤን ስታዲየም ከሰራ ተቋም ባለሙያ አምጥተናል። ኮንትራቱን የምናስተዳድረው እኛ ስላልሆንን ለስፖርት ኮሚሽን ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እና ብሔራዊ ቡድኑ እንዲመለስ የበኩላችንን አድርገናል። ዛሬ ጠዋት ወደ ታንዛኒያ ያመራው ብሔራዊ ቡድናችን ከትኬት ውጪ 1.3 ሚሊዮን ብር ነው ወጪ የሚደረግበት። እዚህ ቢጫወት ኖሮ ይሄንን ወጪ አናወጣም ነበር። አንዳንድ ሰው ይሄንን ለምን ስታዲየም አትሰሩበትም ይላል። ግን አስቂም ነው። በዚህ ብር ስታዲየም አይሰራም። አቅም ኖሮን የተጀመሩትን ስታዲየሞች ጨርሰን መስጠት ብንችል ደስ ባለኝ። ቴክኒካል የሆኑ ነገሮች እንዲሟሉ ካፍ የሰጠውን ነገር አስረክበናል። ከምንም በላይ የተፈቀደ ሜዳ ስለሌሌን ዋጋ እየከፈለ ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው። ህዝባችንም ብሔራዊ ቡድኑን መመልከት አልቻለም። እንደ ባዕድ በቴሌቪዥን ነው የሚያየው። እርሱም የመተላለፍ ዕድሉ ከተገኘ ነው። ከማንም በላይ እኛን ያመናል። በእርግጠኝነት ግን የተጀመሩት ስታዲየሞች ካለቁ ትልልቅ ውድድሮችን ማስተናገድ እንጀምራለን። ቢያንስ ግን ቶሎ አንዱ ማለቅ አለበት። ለማለቅ ተጠግቶ ያለው የባህር ዳር ስታዲየም ነው። እርሱን በቅርበት እየተከታተልን ደጅ መጥናቱን እንቀጥላለን።